ስለ ካንሰር ጥቂት ነገር

ካንሰር የትኛዉንም የሰዉነት አካል የሚያጠቁ በሽታዎች ግሩፕ መጠሪያ ጠቅለል ያለ ስም ነዉ፡፡

ካንሰር ማለት በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ጥቃቅን ህዋሶች (በጤና ግዜም ሰውነታችን የተገነባው ከነሱ ነው) አለአግባብ ማደግ እና መስፋፋት ነዉ፡፡

በሰውነታችን ክፍል ባለች አንዲት ህዋስ ወይም የህዋስ ቡድን ውስጥ የዘረመል ቀውስ ይፈጠራል፡፡በሚሊዮን ብሎም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ህዋሶች ቦታቸውን ለቀው በቅርብም በሩቅም ወዳለ የሰውነታችን ክፍል ይጓዛሉ ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ካንሰር ተከስቷል እንላለን፡፡

የሚነሱበትን የሰዉነት ክፍል በመለየት #ከ2መቶ በላይ የካንሰር ዓይነቶች መኖራቸዉ ይገለጻል፡፡

በጣም የተለመዱ የካንሰር ዓይነት የትኞቹ ናቸዉ?

•የጡት ካንሰር /በሴቶች ላይ በመከሰት የመጀመሪያዉን ቦታ የሚይዝ የካንሰር ዓይነት ነዉ፡፡/

•የፕሮስቴት ካንሰር

•ሜላኖማ/ ከቆዳ ካንሰር ዓይነቶች ከባዱ ነዉ፡፡/

•የአንጀት ካንሰር / በኢትዮጵያ ከጡት እና ማህጸን በር ካንሰር ቀጥሎ በመከሰት 3ተኛዉን ቦታ የሚይዝ ነዉ፡፡/

•የሳምባ ካንሰር እና

•የደም ካንሰር ናቸዉ፡፡

ከላይ የጠቀስናቸዉ የካንሰር ዓይነቶች የሚጠቃለሉት በእነዚህ 5 የካንሰር ክፍሎች ነዉ፡፡

ካርሲኖማ-በብዛት ወደ ህክምና ከሚመጡ የካንሰር ዓይነቶች መሃል አንዱ ነዉ፡፡ በቆዳ፣ በሳምባ፣ በጡት፣ በቆሽት እንዲሁም በሌላ የሰዉነት አካላት ላይ የሚከሰት ነዉ፡፡

ሳርኮማ – ብዙም ያልተለመደ የካንሰር ዓይነት ነዉ፡፡ በአጥንት፣ በጡንቻ፣ በስብ፣ በደም ስሮች፣ በጅማት እንዲሁም በሌሎች ለስላሳ ወይም አገናኝ ህዋሶች ላይ የሚከሰት ነዉ፡፡

ሜላኖማ- ለቆዳችን ቀለም ከሚሰጡ ሴሎቻችን የሚነሳ የካንሰር ዓይነት ነዉ፡፡

ሊምፎማ እና

ሉኪሚያ- ይህ ደግሞ የደም ካንሰር ነዉ፡፡

 ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኘ ተጨማሪ ሀሳብ

ካንሰር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በገዳይነቱ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም፡፡

 • በ2020 የፈረንጆች ዓመት ብቻ ወደ 10 ሚሊየን ሰዉ በካንሰር ምክንያት ህይወቱን አጥቷል፡፡ በህይወት ከሚያልፉ 6 ሰዎች መካከል አንዱ በካንሰር ነዉ የሚሞተዉ፡፡
 • በካንሰር ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል አንድ ሶስተኛዉን ድርሻ የሚይዘዉ ምክንያት የሲጃራ ማጤስ፣ ከፍተኛ የሰዉነት ክብደት፣ አልኮል መጠቀም፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ አጠቃቀማችን ያነሰ መሆን እና በቂ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ናቸዉ፡፡
 • ካንሰር አምጪ የሆኑ እንደ ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ እና ሄፓታይተስ ያሉ ኢንፌክሽኖች በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ አገራት ላይ ለሚከሰት የካንሰር ህመም 30 በመቶ ድርሻዉን ይወስዳሉ፡፡
 • አብዛኞቹ የካንሰር ዓይነቶች በግዜ ከተደረሰባቸዉ በህክምና መዳን የምንችላቸዉ ናቸዉ፡፡

በ2020 በተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች እንደ አዲስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር እናጋራችሁ፡፡

 • በጡት ካንሰር እንደ አዲስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2.26 ሚሊየን ነበር፡፡
 • በሳምባ ካንሰር 2.21 ሚሊየን ሰዎች፡፡
 • በአንጀት ካንሰር 1.9 ሚሊየን ሰዎች፡፡
 • በፕሮስቴት ካንሰር 1.4 ሚሊየን ሰዎች፡፡
 • በቆዳ ካንሰር 1.2 ሚሊየን እንዲሁም፤በጨጓራ ካንሰር ደግሞ 1 ሚሊየን አዳዲስ ሰዎች ተይዘዋል፡፡

በ2020 የብዙ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈዉ የካንሰር በሽታ ዓይነት የሳምባ ካንሰር ነበር፡፡

 • በሳምባ ካንሰር በሽታ 1.8 ሚሊየን ሰዎች ህይወታቸዉን አጥተዋል፡፡
 • ሁለተኛዉ የአንጀት ካንሰር ሲሆን የ9መቶ16 ሺህ ሰዎችን ህይወት ነጥቋል፡፡
 • በጉበት ካንሰር ደግሞ 8መቶ30 ሺህ ሰዎች ህይወታቸዉን አጥተዋል፡፡
 • 7መቶ 69ሺህ ሰዎች በጨጓራ ካንሰር ህይወታቸዉን ሲያጡ፤ የጡት ካንሰር ደግሞ የ6መቶ85 ሺህ ሰዎችን ህይወት ነጥቋል፡፡

በየዓመቱ ወደ 4መቶ ሺህ ህጻናት በካንሰር ይያዛሉ፡፡ የተለመዱ የካንሰር ዓይነቶች ከአገር አገር የሚለያዩ ቢሆኑም የማህጸን በር ካንሰር ግን በ23 አገራት የተለመደ ዓይነት የካንሰር ህመም መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

የካንሰር ህመም በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉን ሰዎች በማጥቃት የጡት ካንሰር የመጀመሪያዉን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በአገራችን በካንሰር ከሚከሰቱ ህመሞች 30.2 በመቶዉን የሚይዘዉ የጡት ካንሰር ነዉ፡፡

በሁለተኛነት የማህጸን በር ካንሰር ሲሆን ከአጠቃላይ የካንሰር ህመም ዉስጥ 13.4 በመቶ ድርሻዉን ይወስዳል፡፡

የትልቁ አንጀት ካንሰር ደግሞ 5.7 በመቶዉን ድርሻ በመያዝ በሶስተኝነት ተቀምጧል፡፡

እስከዳር ግርማ

ሚያዚያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

ኤትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጲያዊያን

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply