ስማይል ትሬን “ሙቪንግ ስማይል” የተሰኘ ባቡር መሰል መኪና በማዘጋጀት አገር አቀፍ የከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጉዞ ማስጀመሩን አስታወቀ

ዕረቡ ጥቅምት 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ስማይል ትሬን ከሰን ኢኮ አርት ፎር ሶሻል ደቨሎፕመንት ጋር በመተባበር በአይነቱ የተለየና “ሙቪንግ ስማይል” የተሰኘ የአስፋልት ላይ ባቡር መሰል መኪና በማዘጋጀት፤ አገር አቀፍ የከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጉዞ በይፉ ማስጀመሩን በዛሬው ዕለት አስታውቋል።

ይህ አገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ የጉዞ መርሃ ግብር፤ አይንን በሚስብ መልኩ ለማንኛውም እድሜ ክልል፣ ሀይማኖት እና ባህል በቀላሉ መልዕክትን ለማስተላለፍ ታቅዶ መዘጋጀቱን የሰን ኢኮ አርት ፎር ሶሻል ደቨሎፕመንት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኤፍሬም በቀለ ተናግረዋል።

“ሙቪንግ ስማይል” በተሰኘው ባቡር መሰል መኪናም ከሰን ኢኮ ሰርከስ ቡድን እና ሌሎች አዝናኝ እንዲሁም ትምህርት አዘል መርሃ ግብሮች ጋር ታጅቦ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች የመዞር እቅድ መያዙንም ኤፍሬም ጨምረው ገልጸዋል።በዚሁ ባቡር መሰል መኪና ላይም ጎልቶ የሚታይ ‘አቢቲ’ የሚባል የፕሮጀክቱ መለያ ገጸ ባህሪ እንደሚገኝም ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ይህም ገጸ ባህሪ ከከንፈር መሰንጠቅ ጋር አብሮ የተወለደ ህጻን ልጅ እንደሆነና ሌሎች እንደሱ ላሉ ህጻናት ጥንካሬን፣ ብርታትን እንዲሁም አሸናፊነትን በታሪክ አዋዝቶ እያስተማረ የሚገኝ የፕሮጀክቱ አንድ አካል መሆኑ አስረድተዋል።ስማይል ትሬን በኢትዮጵያ ከ2007 ጀምሮ ከ32 ሺሕ ህጻናት እና ወጣቶች በላይ የነፃ ቀዶ ጥገና ህክምና እና አገልግሎት መስጠቱን የገለጹት በምስራቅ አፍሪካ የስማይል ትሬን ረዳት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ቤተል ሙሉጌታ ሲሆኑ፤ ከዚህም በተጨማሪም ድርጅቱ ከከንፈር እና ላንቃ ጋር ተያይዞ ነጻ የጥርስ ህክምና፣ የአመጋገብ ምክር፣ የንግግር ህክምና (speech therapy)፣ የማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ እና ሌሎችም አገልግሎቶችን የያዘ ኹሉን አቀፍ የአገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አክለውም ስማይል ትሬን በአገር ውስጥ ለሚገኙ የግል እና የመንግስት ሆስፒታሎች እና ሀኪሞች የቀዶ ጥገና ህክምና ስልጠናዎችን በመስጠት ዘላቂ የሆነ መፍትሄዎችን እዚሁ ባሉ የጤና ባለሙያዎች እንዲሰጥ እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።በ”ሙቪንግ ስማይል” ፕሮጀክትም የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ህክምና ቡድን በመፍጠር፤ ወላጆች እርስ በርሳቸው ልምድ መቅሰሚያ መድረክና በባለሙያ የሚመራ የምክክር አገልግሎት መዘጋጀቱን የገለጹት ዶ/ር ቤተል፤ በተጨማሪም ጥበባዊ አቀራረቦችን እንደዋና ግንኙነት መፍጠሪያ አርጎ በመጠቀም ማህበሰረቡ ስለ ከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በመስራት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ሰፋ ባለ መልኩ በዚህ አገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጉዞ፤ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ላይ በመዘዋወር ስለ ከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ ግንዛቤ ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ስማይል ትሬን(Smile Train) በአለማችን ትልቁ የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ጋር ለተወለዱ ህጻናት የማስተካከያ ቀዶ ጥገና የሚሰጥ የአሜሪካ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፤ ከ1999 ጀምሮ በአለማችን ላይ 1.5 ሚልዮን ህጻናት ቀዶ ጥገና በነፃ አድርጓል።በኢትዮጵያ ከ2007 አገልግሎት መስጠት የጀመረው ድርጅቱ፤ እስካአሁን ከ32 ሺሕ ህጻናት እና ወጣቶች በላይ የነፃ ቀዶ ጥገና ህክምና እና አገልግሎት መሥጠቱ ተገልጿል።

ሰን ኢኮ አርት ፎር ሶሻል ደቨሎፕመንት በአሁኑ ሰዓት ከስማይል ትሬን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ‘ዘ ሙቪንግ ስማይa’ (The Moving Smile) የተሰኘ ፐሮጀክት ቀርጾ ለአለፈው አንድ ዓመት ያህል በመተግበር ይገኛል።የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ጋር ተያይዞ ችግር ያለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎችም፤ ድርጅቱ የነጻ ጥሪ ማዕከል 9889 ላይ በነጻ በመደወል ለህክምናው መመዝገብ፣ መረጃ ማግኘት እና መማር እንደሚችሉ በመድረኩ ተገልጿል።

በተጨማሪም በማህበራዊ ሚዲያ @themovingsmile ወይም ⓜsunekoethiopia ላይ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻል ተነግሯል።
______

The post ስማይል ትሬን “ሙቪንግ ስማይል” የተሰኘ ባቡር መሰል መኪና በማዘጋጀት አገር አቀፍ የከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጉዞ ማስጀመሩን አስታወቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply