You are currently viewing ስራቸውን በለቀቁ የኢሰመኮ ኮሚሽነር ምትክ አዲስ ኃላፊ ሊሾም ነው 

ስራቸውን በለቀቁ የኢሰመኮ ኮሚሽነር ምትክ አዲስ ኃላፊ ሊሾም ነው 

በናሆም አየለ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ካሉት አምስት ኮሚሽነሮች መካከል አንዷ በነበሩት የሴቶች እና ህጻናት መብቶች ዘርፍ ኃላፊ ምትክ፤ አዲስ ኮሚሽነር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሊሾም ነው። ለተተኪ ኮሚሽነርነት ዕጩ የሚሆኑ ግለሰቦች ጥቆማ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት እንደሚካሄድም ተገልጿል። 

የዕጩ ጥቆማው መጀመሩን ዛሬ ሰኞ ሚያዚያ 7፤ 2016 ያስታወቀው፤ ይህንኑ ሂደት እንዲያከናውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ ነው። ሰባት አባላት ያሉበትን ይህን ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ በሰብሳቢነት የሚመሩት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ናቸው።

በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት በተሰጠው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን የማቋቋም ስልጣን የተሰጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በተቋሙ በኮሚሽነርነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችን የመሾም ኃላፊነትም ተጥሎበታል። በ2012 ዓ.ም. የተሻሻለው የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ መስሪያ ቤቱ የልዩ ልዩ የሰብዓዊ መብቶች ዘርፍ ጉዳዮችን የሚመሩ ከአራት ያላነሱ ኮሚሽነሮች እንደሚኖሩት ይደነግጋል።

አሁን በስራ ላይ ያሉት አምስት ኮሚሽነሮች ሹመት በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው በሰኔ 2013 ዓ.ም. ነበር። የሴቶች እና ህጻናት መብቶች በኮሚሽነርት እንዲመሩ በወቅቱ ተሹመው የነበሩት መስከረም ገስጥ፤ ስራቸውን “በገዛ ፍቃዳቸው የለቀቁት” ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ በኃላፊነት ካገለገሉ በኋላ መሆኑን ከኢሰመኮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

ላለፉት ስድስት ወራት ያለ ኃላፊ የቆየውን የሴቶች እና ህጻናት መብቶችን ዘርፍ ስራ ደርበው ሲሰሩ የቆዩት፤ በተቋሙ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ መሆናቸውንም ኮሚሽኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። ስራቸውን የለቀቁትን የኢሰመኮ ኮሚሽነር የሚተኩ ዕጩዎችን ለማቅረብ የተቋቋመው ኮሚቴ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ፤ ዕጩዎችን የማስመረጥ፣ የመለየት እና በፓርላማ የማሾም ስራውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ማቀዱን አስታውቋል። 

ለኮሚሽነርነት የሚጠቆሙ ዕጩዎች ሴት መሆን እንዳለባቸው የኮሚቴው ጸሀፊ ወ/ሮ ባንቺ ይርጋ መለሰ በዛሬው መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ይህ የሆነበት ምክንያትም ዘርፉ የሴቶች እና ህጻናትን መብቶች ጉዳይ የሚመለከት በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ጸሀፊዋ አስረድተዋል። ለዕጩነት የሚጠቆሙ ግለሰቦች፤ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ መሆን እንዳለበትም አክለዋል። 

ተጠቋሚዎቹ “በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ” እና “በህግ ወይም አግባብነት ባለው ሌላ ሙያ የሰለጠነ ወይም በልምድ ሰፊ ዕውቀት ያካበቱ” መሆን እንደሚገባቸውም በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። “የየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባል የሆኑ” ግለሰቦች በዕጩነት መጠቆም እንደማይችሉም ተገልጿል። 

የዕጩዎች መስፈርቱ “የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኝነት” እንደሚጠይቀው ሁሉ፤ ተጠቋሚዎቹ “ከደንብ መተላለፍ ውጭ በሌላ የወንጀል ጥፋት ተከስሰው ያልተፈረደባቸው” መሆን እንዳለባቸው አስፍሯል። ዕጩዎች “ስራውን ለመስራት የሚያስችል የተሟላ ጤንነት” ሊኖራቸው እንደሚገባም በመስፈርትነት ተቀምጧል። 

እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉ ዕጩዎች፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የ ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ ከዛሬ ጀምሮ  እስከ ሚያዚያ 22፤ 2016 ድረስ መጠቆም እንደሚቻል ወ/ሮ ባንቺ ይርጋ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢሜይል አድራሻ፣ በዋትስ አፕ እና ቴሌግራም አማካኝነት ዕጩዎችን መጠቆም እንደሚቻል በዛሬው መግለጫ ላይ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply