ሶማሊያ በዋና ከተማዋ የፊት ማስኮች እንዳይደረጉ ከለከለች፡፡

ሶማሊያ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ከደህንነት ጋር በተያያዘ ምክንያት የፊት ማስኮች እንዳይደረጉ አዛለች፡፡

የሞቃዲሾ ከተማ አስተዳደር ቃል አቀባይ ሳላህ ዲሄሪ በከተማዋ ማስኮች ማንነትን ለመደበቅ እንዲሁም የወንጀል ተግባራትን ለማከናወን ጥቅም ላይ እየዋሉ በመሆኑ ክልከላዉ መድረጉን ገልጸዋል፡፡

ክልከላዉ በኮቪድ-19 ምክንያት በከተማዋ የተስፋፋዉን ማስክ የመጠቀም ልማድን ተከትሎ የመጣ ነዉ ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ባለስልጣናቱ ኮፍያዎችን ማድረግ እንዲሁም ደግሞ በህዝብ ትራንስፖርት ዉስጥ ምንም ዓይነት መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ክልከላዎችን አስቀምጠዋል፡፡

ክልከላዉ ታዲያ በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚጠቀሙትን ‹‹ሱናህ›› የተሰኘ ባህላዊ ኮፍያን ጭምር የሚያካትት ነዉ፡፡

ይህን ዉሳኔ ለመተግበር የተወሰነዉ በቅርቡ በደህንነት ስብሰባ ላይ በፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ የተነሳዉን ሀሳብ በመከተል ነዉ ተብሏል፡፡

ሶማሊያ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ምክንያት በሚደርስባት ጥቃት እና ማስፈራራት በደህንነት ስጋት ዉስጥ ያለች አገር ናት፡፡

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በታጣቂ ቡድኑ ላይ በነሀሴ 2022 ባስጀመሩት ጥቃት ምክንያት ደግሞ አልሸባብ ጥቃቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡

እስከዳር ግርማ

የካቲት 06 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply