ሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ በሁለት ወራት ገደማ የመጨረሻውን ሥምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል!ለሶማሌላንድ እውቅና ለኢትዮጵያ የባሕር ኃይል የጦር ሠፈር በኪራይ የሚሰጠው ሥምምነት በሁለት ወ…

ሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ በሁለት ወራት ገደማ የመጨረሻውን ሥምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል!

ለሶማሌላንድ እውቅና ለኢትዮጵያ የባሕር ኃይል የጦር ሠፈር በኪራይ የሚሰጠው ሥምምነት በሁለት ወራት ገደማ ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ለባሕር ኃይል የጦር ሠፈር ልትከራይ የምትችላቸው ሦስት አማራጭ ቦታዎች መለየታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ዲፕሎማቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢአብዲ የተፈራረሙት “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት” በመጪዎቹ ወራት ወደ ተግባር ይሸጋገራል ብለው እየጠበቁ ነው።

የመግባቢያ ሥምምነቱ ከአራት ወራት በፊት ታህሳስ 22 ቀን 2016 ሲፈረም ድርድሩ በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ የመግባቢያ ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን እና የቴክኒክ ኮሚቴዎች መታጨታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“ነገሮች በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ነበር” ያሉት ዶክተር ኢሳ ካይድ በረመዳን የጾም ወር ወቅት ሒደቱ ቢቀዛቀዝም በመጪዎቹ ወራት ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ሥምምነቱን ወደ ተግባር የሚያሸጋግር የመጨረሻውን ሥምምነት ሊፈራረሙ እንደሚችሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“ሁሉም ነገር ሁለቱ ቡድኖች በሥምምነቱ ላይ ለመደራደር ሲገናኙ ይወሰናል” ያሉት ዶክተር ኢሳ “የሕግ እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች አሉ። በመጪዎቹ ወራት ምን አልባትም በሁለት ወራት ገደማ ይጠናቀቃል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ሳዓድ አሊ ሽሬ ሥምምነቱ ተፈርሞ “ዕውቅና ስናገኝ በዓለም አቀፍ መድረክ ድምጽ ስለሚኖረን በፖለቲካ ረገድ ጠቃሚ ነው” ሲሉ ተስፋቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ሶማሌላንድ የምታገኘው ዕውቅና “ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድ፣ ለጉዞ እና በዕድገት በር ስለሚከፍት በኤኮኖሚ ረገድ ጠቃሚ ይሆናል” የሚሉት የፋይናንስ ሚኒስትሩ ሶማሌላንድ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት እንድትተሳሰር ይረዳታል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

“ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ መበደር እንችላለን” ሲሉ የተናገሩት ዶክተር ሳዓድ አሊ “በዕውቅናው ምክንያት እጅግ በርካታ በሮች” ለሶማሌላንድ እንደሚከፈቱ ይጠብቃሉ።

ሥምምነቱ ከተፈረመ ሶማሌላንድ ዕውቅና ስታገኝ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል የጦር ሠፈር የምታቋቁምበትን ወደብ በኪራይ ታገኛለች።

ሶማሌላንድ 850 ኪሎ ሜትር ገደማ በሚረዝመው የባሕር ዳርቻ ኢትዮጵያ ልትከራይ የምትችልባቸውን ሦስት ቦታዎች በአማራጭነት መለየታቸውን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ አረጋግጠዋል።

“የለየናቸው የተወሰኑ ቦታዎች አሉ። ከኢትዮጵያ አቻዎቻችን ጋር ከተገናኘን በኋላ አንዱ ይመረጣል” ያሉት የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተለዩትን ሦስት ቦታዎች ስሞች ከመናገር ተቆጥበዋል።

ኢትዮጵያ የደርግ ሥርዓተ መንግሥት ወድቆ ኤርትራ ነጻነቷን ስታውጅ የፈረሰውን የባሕር ኃይል መልሳ ያቋቋመችው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በፈረንሳይ እና የቀድሞ የባሕር ኃይል መኮንኖች ድጋፍ የባሕር ኃይሉን በአዋጅ መልሶ ያቋቋመው በ2011 ነበር።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply