You are currently viewing ሶስት የሜዳይ እና ሁለት የኒሻን ሽልማት አይነቶችን የሚያቋቁም የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ 

ሶስት የሜዳይ እና ሁለት የኒሻን ሽልማት አይነቶችን የሚያቋቁም የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ 

በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ በተለያዩ መስኮች “የላቀ ስራ የሰሩ” ግለሰቦችን እና ሌሎች አካላትን እውቅና እና ሽልማት ለመስጠት የሚያስችል የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። አዋጁ ለላቀ የስራ ፈጠራ፣ አርአያነት ላለው የሲቪል አገልግሎት እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ስራ ለሰሩ ሰዎች እና አካላት የሚበረከቱ ሶስት የተለያዩ ሜዳዮችን እንዲሁም ሁለት የክብር ኒሻን አይነቶችን የሚያቋቁም ነው። 

ሜዳይ እና ኒሻን “በአብዛኛው ሳንቲም በሚመስል ብረት ላይ ጌጥ በመቅረጽ ወይም በማተም፤ የማዕረግ አርማ በማድረግ አሊያም ቃላትን፣ ድርጊትን፣ ኩነትን በሚገልጽ መልኩ በመቅረጽ” የሚሰጡ የክብር ሽልማቶች ናቸው። በኢትዮጵያ ከአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ሜዳዮችን የመስጠት ልማድ የነበረ ቢሆንም፤ ሽልማቶቹ በህግ ደረጃ ተቋቋመው ሲሰጡ የነበረው በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት እንደነበር ለፓርላማ በቀረበ የአዋጅ ማብራሪያ ላይ ተጠቅሷል። 

አሁን በስራ ላይ ባለው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት “በህግ መሰረት” ኒሻኖችን እና ሽልማቶችን እንደሚሰጥ ቢደነገግም፤ ይህንኑ የሚመራ ህግ እስካሁን ሳይወጣለት ቆይቷል። እስካሁን ድረስ “በተበታተነ ሁኔታ” ሲከናወን የቆየውን የሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት አሰጣጥ “ህጋዊ ስርዓት የሚያበጅለት” እንደሆነ የተነገረለት የአዋጅ ረቂቅ፤ በአምስት ክፍሎች እና በ29 አንቀጾች ተከፋፍሎ ተዘጋጅቷል። 

ፎቶ፡ ከብልጽግና ፓርቲ የፌስቡክ ገጽ የተገኘ

ከወታደራዊ እና ፖሊስ አገልግሎት ውጪ ያሉ አካላት ላይ ብቻ ተፈጻሚ እንዲሆን የተዘጋጀው ይህ አዋጅ፤ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 3፤ 2016 ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ለዝርዝር ዕይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቷል። የአዋጅ ረቂቁ በውስጡ ከያዛቸው ድንጋጌዎች ውስጥ ስለ ሜዳይ፣ ኒሻን አይነቶች እንዲሁም ስለሚሰጡበት ሁኔታ የሚያትቱት ይገኙበታል። በአዋጁ መሰረት ከሚቋቋሙ የሜዳይ አይነቶች በመጀመሪያ ረድፍ የተቀመጠው፤ “የላቀ የፈጠራ ስራ” ላከናወኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ድርጅቶች የሚበረከተው ነው። 

“ብሔራዊ የላቀ የፈጠራ ስራ ሜዳይ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሽልማት፤ በኢትዮጵያ ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ “በተለያዩ ዘርፎች የህብረተሰብን ችግር የፈታ ወይም የሚፈታ እጅግ የላቀ ስራ ለሰሩ” ሰዎች የሚበረከት መሆኑ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። አንድ የፈጠራ ስራ የሰራ ሰው ይህን ሽልማት ሊሸለም የሚችለው፤ “በሀገሪቱ አግባብነት ባላቸው የፓተንት ወይም የቅጂና ተዛማጅ ህጎች መሰረት ፓተንት ወይም የቅጂ መብት የተሰጠው” እንደሆነ ብቻ መሆኑን በአዋጁ ማብራሪያ ላይ ተቀምጧል። 

በአዲሱ አዋጅ የሚቋቋመው ሁለተኛ የሜዳይ አይነት፤ “ብሔራዊ የህዳሴ ሜዳይ” የሚል ስያሜ ያለው ነው። ይህ ሜዳይ የሚሰጠው፤ በሳይንስና ምርምር፣ በቴክኖሎጂ፣ በስነ ጥበብ፣ በስፖርት ወይም በተለያዩ ዘርፎች “ለሀገር፣ ለህዝብ ወይም በአጠቃላይ ለሰው ልጆች እጅግ የላቀ ስራ ለሰሩ” ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ድርጅቶች መሆኑ ተገልጿል። 

ፎቶ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

“ብሔራዊ የላቀ ሲቪል አገልግሎት ሜዳይ” የተባለው ቀሪው የሜዳይ አይነት፤ “የስራ ዲሲፕሊን ጠብቀው፣ በታታሪነት እና በታማኝነት በማገልገል የላቀ ስራ የሰሩ” የመንግስት ሰራተኞች የሚሸለሙት እንደሆነ በአዋጅ ረቂቁ ተመልክቷል። ይህ የሜዳይ ሽልማት “ለረጅም ጊዜ አርአያነት ያለው አገልግሎት ሰጥተው” በጡረታ ወይም በሌላ ምክንያት የመንግስት መስሪያ ቤትን ለለቀቁ ወይም በስራ ላይ እያሉ ለፈጸሙት ሀገርን የማገልገል ተግባር “እውቅና እና ክብር የሚሰጥበት ነው” ተብሏል።

እነዚህን የሜዳይ አይነቶች የተሸለሙ ግለሰቦች፤ “ልዩ መብቶች” እንደሚያገኙ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተደንግጓል። አንድ ተሸላሚ ደመወዝ ካለው የደመወዙ 25 በመቶ፤ ጡረተኛ ከሆነ ደግሞ የጡረታ አበሉ 40 በመቶ እንደሚጨመርለት በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። ተሸላሚው ደመወዝ ከሌለው፤ አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጣ መመሪያ የሚወሰን የገንዘብ መጠን “በስጦታነት” እንደሚሰጠው ተጠቅሷል። 

የሜዳይ ተሸላሚዎች ከሚያገኟቸው ልዩ መብቶች ውስጥ “በመንግስት የጤና ተቋማት ነጻ የህክምና አገልግሎት ማግኘት” የሚለው ተካትቷል። የሜዳይ ተሸላሚዎች በመንግስት የትምህርት ተቋሞች “ቅድሚያ የትምህርት ዕድል ይሰጣቸዋል” የሚለውም “በልዩ መብትነት” ተዘርዝሯል። ተሸላሚዎች በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የተፈረመ “መታወቂያ እና ሰርተፊኬት” የሚሰጣቸው መሆኑ፤ ሌላው “በልዩ መብትነት” የተካተተ ድንጋጌ ነው። 

ፎቶ፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌስቡክ ገጽ የተገኘ

የአዋጅ ረቂቁ ከሜዳዮች በተጨማሪ “የኢትዮጵያ ታላቅ ክብር ኒሻን” እና “የአፍሪካ ታላቅ ክብር ኒሻን” የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን የክብር ሽልማቶችን የሚያቋቁሙ ድንጋጌዎችን በውስጡ ይዟል። የኒሻን ሽልማቶች በአብዛኛው “ሀገራት ለሀገር መሪዎች እና በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ግለሰቦች የሚበረከቱ” መሆናቸውን አዋጁን ለማብራራት የቀረበው ሰነድ አትቷል።  

በዚሁ ማብራሪያ ላይ “የኢትዮጵያ ታላቅ ክብር ኒሻን” በሀገር ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ “በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ዘርፎች እንዲሁም በዲፕሎማሲ መስክ እጅግ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ” ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ድርጅቶች የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል። “የአፍሪካ ታላቅ ክብር ኒሻን” ደግሞ “በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያ፣ ማህበራዊ ዘርፎች” አህጉራዊ ችግር ፈቺ ስራ ላበረከተ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት የሚሰጥ መሆኑ ተጠቅሷል። ይህ የኒሻን ሽልማት በአፍሪካ ሀገራት መካከል “መልካም ወዳጅነት እና ዘላቂ ትስስር እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ” ግለሰቦች እና አካላትም የሚሰጥ መሆኑን የአዋጅ ረቂቁ አክሏል። 

እነዚህን የኒሻን ሽልማቶች ያገኙ ግለሰቦች፤ በስማቸው “መንገድ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ ህንጻ ወይም ተመሳሳይ ተቋም እንደሚሰየምላቸው” በአዋጅ ረቂቁ ተደንግጓል። የኒሻን ተሸላሚዎቹ፤ በብሔራዊ በዓላት የአከባበር ስነ ስርዓት ላይ በሚዘጋጅላቸው ቦታዎች ላይ ይቀመጣሉ። የኒሻን ተሸላሚዎች ሜዳይ የሚሰጣቸው ሰዎች የሚያገኟቸው የደመወዝ፣ የገንዘብ ስጦታ፣ የትምህርት ዕድል እና የህክምና አገልግሎት በተመሳሳይ መልኩ ተጠብቆላቸዋል።  

ፎቶ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ሜዳይ፣ ኒሻን ወይም ሽልማት ለማግኘት የሚያበቃ ተግባር ፈጽሞ ለሞተ ሰው፤ በአዲሱ አዋጅ መሰረት አግባብነት ያለው ሽልማት እንደሚዘጋጅለት በህግ ረቂቁ ላይ ተመልክቷል። በአዋጁ መሰረት የሚዘጋጀው ሜዳይ፣ ኒሻን ወይም ሽልማት “ለሟቹ ተሸላሚ ታላቅ ልጅ ወይም በልጆቹ ዕድሜ ቅደም ተከተል የሚሰጥ” ይሆናል። 

ሁለት ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ሜዳይ ወይም ኒሻን የተሸለመ ግለሰብ ከእነዚህ ዕውቅናዎች በተጨማሪ በማንኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ “አግባብነት ባለው ስፍራ ሀውልት ሊቆምለት እንደሚችል” በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል። የሀውልቱ አይነት፣ መጠን፣ ይዘት እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች የሚወሰኑት፤ ወደፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚወጣ መመሪያ መሆኑም ተጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply