ሸዋ ፋኖ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ሰብሳቢዎችን፣የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንና ስራ አስፈጻሚዎችን አስመረጠ፤ የመተዳደሪያ ደንቡንም አጽድቋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 21 ቀን 20…

ሸዋ ፋኖ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ሰብሳቢዎችን፣የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንና ስራ አስፈጻሚዎችን አስመረጠ፤ የመተዳደሪያ ደንቡንም አጽድቋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 21 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ሸዋ ፋኖ ታህሳስ 20 ቀን 2014 ከተለያዩ አካባቢዎች በርካታ አባላት በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤውን በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል። በጉባኤው መክፈቻም አሸባሪዎችንና ወራሪዎችን በተለያዩ ጊዜያትና አውደ ውጊያዎች ሲፋለሙ በክብር ለተሰው ጀግኖች ሰማዕታት የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጎላቸዋል። ሸዋ ፋኖ በመድረኩ ላሉ ለጉባኤ አባላቱ በትኖ ሀሳብ እንዲንሸራሸርበት ብሎም በመድረኩ ተነቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበትንና ቢካተቱ ጥሩ ናቸው የተባሉ ሀሳብ አስተያየቶች የተሰጡበት የማህበሩ ህገ ደንብን በ82 ድጋፍ፣ በ4 ተቃውሞ አጸድቋል። ከጠቅላላ ጉባኤው አባላት ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችም መድረኩን የመሩት ዶ/ር ወንዶሰን አሰፋ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። በመቀጠልም 3 የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ማለትም:_ 1) ረ/ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፣ 2) ፋኖ ተሾመ አየለ/ተሼ ባላገሩ እና ሌላ አንድ ሰው ተመርጠው የማዕከላዊ ኮሚቴውን ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እየመሩ ጉባኤ ሲኖር ብቻ ተገኝተው የሚሰበስቡ 3 ሰብሳቢዎችን አስመርጠዋል። በእለቱም:_ 1) ዶ/ር ወንዶሰን አሰፋ_ ሰብሳቢ 2) አቶ ቴዎድሮስ ከበደ _ምክትል ሰብሳቢ እና 3) አቶ አዳም _የሸዋ ፋኖ ጸሀፊ ሆነው በጉባኤው ተመርጠዋል። ጠቅላላ ጉባኤው ማዕከላዊ ኮሚቴውን መርጧል፤ ማዕከላዊ ኮሚቴው ደግሞ ከመካከሉ ስራ አስፈጻሚዎችን በመምረጥ የስራ ድልድል አድርጓል፤ የማዕከላዊ ኮሚቴው ቁጥር በአባል ቅ/ጽ/ቤት ቁጥር ይሆናል። የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢ ዶ/ር ወንዶሰን ሁለት ተጨማሪ አባላትን ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ይሰይማል በሚለው ህገ ደንብ መሰረት ፋኖ ተስፋ ሽቱን እና ፋኖ ተስፋዬ ጌታቸውን ጨምረው 15 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም 3 የኦዲትና ኢንስፔክሽን ተጠሪዎችን አስመርጠዋል። በአጠቃላይ ሸዋ ፋኖ ታህሳስ 20 ቀን 2014 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው 15 አባላት ያሉት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ሰይሟል። እነሱም የስራ ክፍፍል አድርገው ባስታወቁት መሰረት:_ 1) ዶ/ር ታደሰ ተ/ስላሴ_ሊቀመንበር፣ 2) አበባው ሰለሞን_ ም/ሊቀመንበር፣ 3) ተስፋ ሽቱ_ጸሀፊ ሆነው ተመርጠዋል። ጉባኤው ካሁን ቀደም ሸዋ ፋኖን በሰብሳቢነት በመምራት የቆዩትን ፋኖ ሽመልስ ንጉሴንና ሌሎችም በኃላፊነት ስሜት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ የቆዩ ስራ አስፈጻሚዎችንና አባላትን አመስግኗል። በጉባኤው የተገኙት ረ/ፕሮፌሰር ሲሳይ “ሸዋ ውስጥ የተለያየ ቡድን እንዲኖር አልፈልግም፤ ሁላችንም የሸዋ ልጆች አንድ ሆነን እንደ ወንድማማች ልክ አጣዬ ሲነካ እንደሚከፋን፣ ልክ ምንጃር ሲነካ እንደሚከፋን፣ ሌላውም ሲነካ እንደሚከፋን ሄደን እዛ ለመሞት ዝግጁ የሆንን ልጆች እስከሆንን ድረስ በሁሉም አካባቢ ያለው ፋኖ ወደ አንድ መምጣት አለበት፤ ሸዋ ላይ ያለው የሚል እምነት አለን፤ አቋም አለን። ለዚህም ወደፊት እንሰራለን፤ ስለዚህ ራሳችሁን ለዚህ ማዘጋጀት አለባችሁ።” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ሲቀጥሉም “ሸዋ ውስጥ ማንም ሰው አኩራፊ መሆን የለበትም፤ ወይም በፋኖ ስም የተለየ አደረጃጀት ይዞ መንቀሳቀስ አለበት ብዬ እኔ አላምንም፤ ምክንያቱም አላማችን ተመሳሳይ ነው። አላማችን ይህንን ህዝብ መከላከል ነው፤ አላማችን የተጋረጠብንን አደጋ አሸንፈን ህይወታችን ሰጥተን መውጣትና ሸዋን፣ አማራን ማስከበር፣ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ ነው።” ሲሉም አክለዋል። በጉባኤው ከተገኙት መካከል ፋኖ ተሾመ አየለ (ተሼ ባላገሩ) “ሸዋ እንደ ሸዋ እግዚአብሔር የአባቶቻችን አምላክ አግዞን በእናንተ ጀግንነት የመጣው ውጤት ተጀመረ እንጅ አላለቀም” ነው ያሉት። አደራ ለማለት የምፈልጋቸው ሲሉ የቀጠሉት ፋኖ ተሾመ የአባቶቻችን ራዕይ ከፍ ብሎ እንዲታይ ካስፈለገ ጠላቶቻችን የሰጡንን የቤት ስራ ከአዕምሮአችን አውጥተነው፣ፍጹም ወንድምነት፣ ፍጹም ደግነት፣ ፍጹም ጀግንነት በተሞላበት መልኩ በመመካከር መስራት እንደሚገባን አሳስበዋል። “በሙሉ ኢትዮጵያን የሚያተርፍ፣ አማራን እንደ አማራ ከፍ የሚያደርግ፣ ከስደትና ከውርደት የሚያድን እሳቤ ይዘን ልንሄድ እንደሚገባም”መክረዋል። ከይፋት ልማት ማህበር የመጡት ሌላኛው አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው “ሸዋ በልኩ አልተሰናዳም፤ አልተዘጋጀም ነበር፤ ነገ ደግሞ አይደለም ራሱን ለሌላው ተርፎ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የሚያስከብር ኃይል ይሆናል” ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ሁሉም ፋኖ ዲሲፒሊን እና የማህበሩን ህግና ደንብ አክብሮ የሸዋን ህዝብ የሚመጥን የአማራን ህዝብ ክብር የሚወክል ፋኖ በሸዋ ተብሎ ስምን የሚያስጠራና የምንኮራበት አደረጃጀት እንዲሆን ከጎናችሁ ነን ብለዋል። ሌሎች የሲቪክ ማህበር አመራሮችና አባላትም ጉባኤው ህገ ደንቡን በማጽደቅ ሰብሳቢዎችን፣ማዕከላዊ ኮሚቴና ስራ አስፈጻሚዎችን በተሳካ መልኩ ለመምረጥ በመቻሉ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። የቀሩ ወረዳዎች እንዲካተቱ እና ከሌሎች አደረጃጀቶች ጋርም በመቀራረብ ወደ አንድ የመምጣት ንግግሩም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከቤቱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። በመጨረሻም ሸዋ ፋኖ ጉልህ ሚና ለነበራቸው ደጋፊዎች፣ ለፋኖ አመራሮችና አባላት የምስጋና እና የእውቅና ሽልማት አበርክቷል። በአሚማ የዩቱብ አድራሻ ይጠብቁ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply