ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመመርመር ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን መጥለፍ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ወይም ሽ…

ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመመርመር ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን መጥለፍ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡

በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ወንጀል ጋር በተያያዘ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገናኛዎችን እና ደብዳቤዎች ለመጥለፍ ለመርማሪዎች ፈቃድ የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።

አዲሱ ረቂቅ በሥራ ላይ ያለውን በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ የሚሽር ነው።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መርማሪ አካል “አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመው” የሚመለከተውን የዐቃቤ ሕግ ተቋም የበላይ ኃላፊ በማስፈቀድ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የመገናኛ እና የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ ይችላል።

መገናኛዎችን እና የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ ከወንጀሎቹ ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ከሚደረጉ የምርመራ ዘዴዎች መካከል ናቸው።

በባንክ ሂሳቦች እና በሌሎች ተመሳሳይ ሂሳቦች ላይ ክትትል ማድረግ፣ የኮምፒውተር ሥርዓቶችን፣ መረቦችን ሰርቨሮችን መለየትም በተመሳሳይ ሌሎች የምርመራ ዘዴዎች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራም (undercover operation) በተመሳሳይ በአዋጁ የተጠቀሰ የምርመራ ዘዴ ነው።

ረቂቅ አዋጁ “መርማሪ አካል አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመው በአካባቢው ያለውን እና የሚመለከተውን የዐቃቤ ሕግ ተቋም የበላይ ኃላፊ በማስፈቀድ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም ማስረጃ ሊሰበስብ ይችላል” ይላል።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በዐቃቤ ሕግ ይሁንታ ብቻ የምርመራ ዘዴዎችን ማከናወን ለመርማሪ አካል አይፈቅድም።

በመርማሪ አካል ጠለፋውን ለማካሄድ የሚጠየቅ የመገናኛ የአገልግሎት አቅራቢ፤ “ጠለፋው በፍርድ ቤት ወይም በዐቃቤ ሕግ የበላይ ኃላፊ የተፈቀደ መሆኑን በማረጋገጥ” ትብብር የማድረግ ግዴታ በረቂቅ አዋጁ ተጥሎበታል።

“የገንዘብ ቅጣት አነስተኛ በመሆኑ አስተማሪ ቅጣት መስጠት የሚያስችል ይዘት አለመኖሩ[ን]” የጠቀሰው የአዋጁ ማብራሪያ የወንጀል ጥፋቶች እና ቅጣቶች ላይ ማሻሻያ እንደተደረገባቸው ያትታል።

በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ በማስመሰል ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ ላይ ይጣል የነበረው የገንዘብ መቀጮ ጣሪያ ከ100 ሺህ ወደ 500 ሺህ ከፍ እንዲል ተደርጓል።

በዚሁ ወንጀል ጥፋተኛ የሚባል ግለሰብ ላይ ይጣል የነበረው የእስር ቅጣት ግን ከዚህ በፊት በነበረበት ከ10 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጥል ተደርጓል።

ሽብርተኝነት በገንዘብ መርዳት ወንጀልም ተመሳሳይ የገንዘብ እና የእስራት መቀጮ የሚጣልበት ሆኖ ተሻሽሏል።

በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ከማስመሰል ተቀጽላ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ይጣል የነበረው ከ5 እስከ 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተሻሽሎ ከ100 እስከ 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ሆኗል።

የእስራት ቅጣቱ ግን ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ሆኖ ቀጥሏል።

ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ወደ ሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ከተመራ በኋላ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ተግባራዊ እንዲሆን ይጸድቃል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሰኔ 04 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply