ቀደም ሲል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተነሱ ግጭቶች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ውሳኔ ተላለፈ።…

ቀደም ሲል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተነሱ ግጭቶች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ውሳኔ ተላለፈ። አሻራ ሚዲያ ታህሳስ፡-30/04/13/ዓ.ም ባህር ዳር ለበርካታ አመታት በሃገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የተነገረው የጥላቻና የመለያየት ርዕዮተ ዓለም ፍሬ አፍርቶ በሀሰት ትርክት ሥሙ፣ ማንነቱና ግብሩ ጥቁር ጥላሸት የተቀባው አማራ በየዘርፉ የሃሰት ትርክት ማወራረጃ ሁኖ መቆየቱ ይታወቃል። ይሄን ተከትሎ የአማራ ተማሪዎች ተፈናቅለዋል፣ ለመጠነኛና ከፍተኛ ጎዳት ተዳርገዋል፣ አስፈላጊ የትምህርት ሰነዳቸው ተቃጥሎና ተዘርፎባቸዋል፣ የአስገድዶ መድፈርና የእገታ ወንጀልም ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በርካታ የአማራ ተማሪወች ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። በሳለፍነው አመት ማለትም በ2012 ዓ.ም ብቻ ከ12 በላይ ተማሪዎች ተገድለዋል። የዚህ አካል የሆነው ከዲምቢ ዶሎ ዩንቨርቲ ግጭት ሸሽተው ሲመለሱ የነበሩ 17ቱ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ያክል ታግተው አድራሻቸው ሳይታወቅ ቀርቷል። የአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) የአማራ ተማሪዎች የሚደርስባቸውን ዘር ተኮር ጥቃት ለመከላከል ማህበሩ ዕውን ከሆነበት ቀን ጀምሮ ለችግሮች ቅደመ-መከላከል፤ ችግሮች ሲፈጠሩም የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የበኩሉን አስተዋጽኦና ድህረ-መከላከል ሲያደርግ ቆይቷል። ማህበሩ በአማራ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸመውን ሁሉን ዓቀፍ ጥቃት በየደረጃው አስቀምጦ ለተፈጻሚነቱ ሲታገልና ለመንግስት ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። ማህበሩ ችግር ከተፈጠረባቸው በየ ከፍተኛ ተቋማቱ ድረስ አመራር ልኮ በመጎብኜት፣ በማንነታቸው ምክንያት የሞቱና የተጎዱ ተማሪዎችን ወደ ቤተሰብ በማድረስ ከፍተኛ ስራ ሰርቷል። ስለጉዳዩም ዝርዝር ጥናት እያዘጋጀ ለሚዲያ አካላትና ለሚመለከተው አካል ሁሉ ተደራሽ አድርጓል። በ2012 ዓ.ም ከደምቢዶሎ የታገቱ 17 ንጹህ የአማራ ተማሪዎችን እና የተፈናናቀሉ ከ35,000 በላይ ተማሪዎችን በማስመልከት ሰልፍ አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው ሁሉ አሳውቋል። በአማራ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃትና መንግስት እያሳየ ስላለው ዝምተኝነት የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት እንዲያውቁት አድርጓል። ማህበሩ መንግስት በአማራ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃት እልባት እንዲሰጥ፣ የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ ይፋ እንዲያደርግና የተፈናቀሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ የሚመለሱበት ዕድል እንዲፈጠር ከጠቅላይ ምኒስቴሩ ጀምሮ ከፌደራልና ከክልል መንግስታት ባለስልጣናት ጋር በየደረጃው ውይይቶችን ማድረጉን መግለጻችን ይታወሳል። የአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) ሲታገልባቸው ከቆየባቸው ጥያቄዎቹ መካከል ተፈናቃይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚል ነበር። ከ22ሺህ በላይ የሚሆኑ የአማራ ተማሪዎች በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጸጥታ ችግር ምክኒያት ከትምህርታቸው ተፈናቅለው ቆይተዋል ማህበራችንም በተከታታይ ከመንግስት ጋር ውይይቶችን በማድረግ ጥያቄዎቹን ሲያቀርብ ቆይቷል። በመጨረሻም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምኒስቴር የማህበሩን ጥያቄ ተቀብሎ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተነሱ ግጭቶች ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ውሳኔ አሳልፏል። ዘጋቢ፡-ጥላሁን ታምሩ

Source: Link to the Post

Leave a Reply