ቅዱስ ሲኖዶሱ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል፤ሲኖዶሱ በምክክር ኮሚሽኑ ቅር መሰኘቱንም አስታውቋል፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባ…

ቅዱስ ሲኖዶሱ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል፤
ሲኖዶሱ በምክክር ኮሚሽኑ ቅር መሰኘቱንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ በርካታ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ውይይት ሲያካሄድ መሰንበቱን ገልጧል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያኗ አንድነት፣ ለሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት፣ ለመንፈሳዊ ዕድገትና ለምእመናን ደኅንነት ትኩረት በመስጠት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፊያለሁ ብሏል፡፡

በዚሁ መሠረት፡-

• በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በሀገራችን መንግሥት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መልካም የሥራ ግንኙነት በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሚመካከር የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፤

• በመላው ሀገራችን በተፈጠሩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና የሰላም ዕጦት በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እንደቀጠለ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከግጭትና ከጥፋት ድርጊት ተቆጥበው የተፈጠረውን አለመግባባትና ግጭት በውይይትና በምክክር እንዲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን አቅርቧል፤

• የሀገራዊ ምክክር ሀገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን እስከአሁን ድረስ በይፋ የቀረበ የተሳትፎ ጥሪ ሳይኖር ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታንና አጀንዳ መረጣ አጠናቆ ወደ ምክክር ትግበራ እየገባ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስን ቅር አሰኝቷል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተሳትፎና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍጻሜ የሚያበቃ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ዜም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply