
ቅዱስ ሲኖዶስ በ7ኛ ቀን ውሎው በአራት አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ። የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ግንቦት 9/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) ሰባተኛ ቀን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል። ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም በአካሄደው ውይይት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቷን ለትውልዱ የታስተምርበት ተቋማት አንዱ መንፈሳዊ ኮሌጆች መሆናቸውን አውስቷል፡፡ እነዚህ ኮሌጆች ወጥ የሆነ ሕግ ሳይኖራቸው የቆየ ሲሆን በቅርቡም በሐዋሳ እና በወልቂጤ የተቋቋሙት ኮሌጆች ባቀረቡት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ውይይት አድርጎ ለሁሉም መንፈሳዊ ኮሌጆች የሚያገለግል ወጥ የሚሆን ሕግ አዘጋጅቶ ማጽደቁን ብፁዕነታቸው ገልጸዋል፡፡ በሌላ አጀንዳ በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በጀርመን ገዳም እንዲኖራት ያቀረበው በጥናት የተደገፈ ሰነድ ጸድቋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተጨማሪ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ አማካኝነት በሰሜን አሜሪካ በካሊፎርኒያ የተመሠረተው የኆኅተ ሰማይ ገዳምን በተመለከተ ጉባኤው የተወያየ ሲሆን ብፁዕነታቸው ገዳሙ የተመሠረተበትን ሰነድ ለጥቅምት ጉባኤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት እንደሚያስረክቡ አስታውቀዋል፡፡ ጉባኤው የአእምሮ ንብረትን የተመለከተ ጉዳይም በስፋት ተወያይቷል። ይህ ኮሚቴ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ የነበረ መሆኑ ታውቆ አሁንም በተጠናከረ መንገድ እንዲሠራ በጀት እንዲያዝለት ተወስኗል፡፡ በሌላ አጀንዳ የምስጢራት መፈጸሚያ የሆነው የጸሎት መጽሐፍም እንዲታተም ተወስኗል፡፡ ጉባኤው የጡረተኞችን አበልን የተመለከተ ጉዳይም ላይ ተወያይቷል። የጡረተኞችን አበልን የተመለከተ ተጠንቶ እንዲቀርብ በታዘዘው መሠረት ጥናቱ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በዕድሜያቸው በቤተክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተው በአነስተኛ ደመወዝ ጡረታ የወጡ ማስተካከያ የሚደረግበት ውሳኔም ተለልፏል፡፡ የዳልሻህ ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ ደናግል አንድነት ገዳምን የተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ የተወያየበት ጉዳይ ነው፡፡ ገዳሙ ከተመሠረተ ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ በዚህ ገዳም ላይ ተነሥቶ የነበረው ችግር በተመለከተ ቅዱስ ተወያይቶበት የውሳኔ ሐሳብ አሳልፏ፡፡ ውሳኔውም እናቶች በጥንት ገዳሙ ሲተዳደርበት በነበረው አሠራር መሠረት እንዲቀጥል ገዳማውያን እናቶች በጥያቄያቸውም መሠረት አምልኮአቸውን እንዲፈጽሙ ውሳኔ ተወስኗል፡፡ ይህም ሰፊ ውይይት ተደርጎበት የእናቶች ገዳም አሠራር መሠረት እናቶች በቆየው ትውፊት፣ በጥያቄያቸው መሠረትም አምልኮታቸውንን እንዲፈጽሙ በመወሰን የዕለቱ ስብሰባ ማጠናቀቁን ለኢኦተቤ ቴቪ በሰጡት ዕለታዊ ማብራሪያ አስታውቀዋል።
Source: Link to the Post