ቅዱስ ሲኖዶስ ዶናልድ ትራምፕ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሰጡትን አስተያየት አወገዘ

ቅዱስ ሲኖዶስ ዶናልድ ትራምፕ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሰጡትን አስተያየት አወገዘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ የታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ያደረጉትን ንግግር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አወገዘ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው የኢትዮጵያን ህዝብ የዘመናት ድህነትና የኑሮ ጉስቁልና አስወግዶ ለሀገሪቱ ብልጽግናም ሆነ ለሕዝቡ ዕድገት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራው ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ መድረሱ ከዚህም በላይ ከሦስት ወራት በፊት የግድቡ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ተደርጐ ለህብረተሰቡ የብስራት ድምጽ በመሰማቱ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን መግለፃቸውን አስታውሷል።
በቀጣይም የግድቡ የዕለት ከዕለት ሥራ እየተከናወነ ህዝቡም የተለመደ ድጋፉን እያደረገ ከሦስት ዓመታት በኋላ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ሲኖዶሱ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
ሆኖም ህዝቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ እና በሙያው የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ በሚገኝበት ወቅት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ግድቡን አስመልክቶ ሀገራትን ወደ ግጭትና አለመግባባት ውስጥ የሚከት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመታዊ ጉባኤው ላይ እንዳለ በሐዘን ተመልክቶታል ብሏል መግለጫው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሆነ ከሌሎች ተመሳሳይ አካላት በኢትዮጵያ ላይ እየተላለፈ ያለው የጥፋት ጥሪ መተዛዘቢያ ከመሆን በስተቀር ጠባቂዋ በሆነው እግዚአብሔርና በህዝቡ አንድነት ተከብራና ተጠብቃ እንደምትኖር ሙሉ እምነታችን ነው ሲልም ገልጿል፡፡
አያይዞም አሁንም በኢትዮጵያ ላይ እየተጐሰመ ያለው የጥፋት ጥሪ ኢትዮጵያን እንደትናንት አባቶች በአንድነት በመከባበርና በመመካከር በመደማመጥም ጭምር መቆም ከቻሉ ከአቅማቸው በላይ የሚሆን ነገር እንደሌለ ከኢትዮጵያውያን ይልቅ የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ የበለጠ ይገነዘቡታል፤ ያውቁታልም ነው ያለው፡፡
ዓለም በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ያጣችው ነገር ሰላምን ነው ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ ሰላም እንደሚታወቀው ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በጋራ ለዓለም ሰላም መቆም ሲቻል ብቻ የሚገኝ ነው ብሏል፡፡
ስለዚህ ይህን የሀገሪቱን ሰላምም ሆነ ጥቅም ሊያሳጣ በሚችል መልኩ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ ያስተላለፉትን የጦርነት ጥሪ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡
መላው የዓለም መንግሥታትና ህብረተሰብም ችግሩን በጥልቀት እንዲገነዘቡት ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው ላይ አሳስቧል።
በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፣ ሀገር የመምራት ኃላፊነት የተጣለባቸው የፌደራልና የክልል መሪዎች እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የትኛውንም የግልና የቡድን አመለካከት ወደጐን በመተው አንድነትን ማጠናከር የሚገባበት ወቅት መሆኑንም አስገንዝቧል።

The post ቅዱስ ሲኖዶስ ዶናልድ ትራምፕ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሰጡትን አስተያየት አወገዘ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply