
ቆንጆዎቹን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል? አቶ ክርስቲያን ታደለ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ የጭቆና አገዛዝ በሰፈነበት ሥርዓት ሕግ ከጉልበት ሎሌነት ያለፈ ዋጋ እንደማይኖረው፤ ግጭት የጨቋኞች የኅልውና ግሉኮስ፥ ሰላም በአንፃሩ የፋሽስት አገዛዙ የኅልውና ሥጋት ስለመሆኑ፤ ገዥው ብልጽግና በመብት ታጋዮች ላይ የሚያደርገው የኃይል እምቃና አፈና ሁነኛ አስረጂ ነው። ያም ሆኖ የጭቆና ኃይል ቁርጠኝነት፣ ዲስፕሊንና የጋራ ግብ ባለው ትግል እንደጉም የሚተን ኃይል ስለመሆኑም የዓለምም ሆነ የቅርብ ጊዜ የአገራችን ተሞክሮዎች ያረጋገጡት እውነት ነው። በኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ያለ ሕዝብ በምልዓት በዚህ ልክ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ ሆኖ ብቻ ሳይሆን የትግሉ ባለቤትና አንቀሳቃሽ ሆኖ ያየሁበት ዘመን የለም። ሕዝብን ደግሞ ታግሎ ያሸነፈ ኃይል በታሪክ ኖሮ አያውቅም። አባቶቻችን ፋሽዝምን በጦር ሜዳ ታግለው ነፃነትን አውርሰውናል። እኛ ልጆቻቸውም ሕዝባችንን ይዘን ፋሽስታዊ አገዛዝን በፖለቲካ ሜዳው በእውቀት፣ እውነትና ጽናት ድል ነስተን፤ ጨቋኞቹን ሳይቀር ራሳቸው ከፈጠሩት የጭቆና ትብታብ ነፃ አውጥተን፤ ኢትዮጵያችንን ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት እናሸጋግራለን። ሕግ አክብረን በዓለም ፊት ርቃናቸውን እናቆማቸዋለን፤ ሰላም ዘምረን የጭቆና ኢያሪኳቸውን እንደረምሰዋለን። ጥላቻቸውን በበጎነታችን እናከሽፈዋለን። በሰፊ ትእግስታችን ትንኮሳቸውን እንሽረዋለን። በአንድነታችን ወጥመዳቸውን እንበጣጥሰዋለን። ሌላው ቀርቶ በዝምታችን ጩኸታም አፋቸውን እንለጉመዋለን። ጭቆና በሰላማዊ ትግል ከነሰንኮፉ ላይመለስ ይመነገላል። እንደሚቻል ብቻ ሳይሆን እንደምንችልም በተግባር እናስመሰክራለን። ምክንያቱም… ትግሉ ኩልል እያለ…የዚህ ዘመን የሰላማዊ ትግል አርበኞች…ቆንጆዎቹ እየመጡ ነው። ምክንያቱም ፋሽዝም ኢትዮጵያን አሸንፏት አያውቅም። ምጡን እርሽው… ፋሽዝም ሲከስም የኢትዮጵያ ትንሳዔ ይጀምራል! ክርስቲያን ታደለ “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post