በሀሰተኛ የብር ኖት ግብይት ሲፈፅሙ የተገኙ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።በበዓላት መዳረሻ ወቅቶች የሚደረግ ግብይት ሃሰተኛ የገንዘብ ዝውውርን መከላከል የሚያስችል ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ…

በሀሰተኛ የብር ኖት ግብይት ሲፈፅሙ የተገኙ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

በበዓላት መዳረሻ ወቅቶች የሚደረግ ግብይት ሃሰተኛ የገንዘብ ዝውውርን መከላከል የሚያስችል ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገጿል፡፡

በለሚ ኩራ እና በልደታ ክፍለ ከተሞች በሀሰተኛ የብር ኖት ግብይት ሲፈፅሙ የተገኙ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አያት አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የሞባይል ስልክ መሸጫ ሱቅ በመሄድ የዋጋ ግምቱ 8 ሺህ ብር የሆነ ሞባይል ስልክ ለመግዛት ተስማምተው ገንዘቡን ቆጥረው በመስጠት ሊያመልጡ የሞከሩ 2 ግለሰቦች አቶ ኤርሚያስ ታደለ የተባሉት የግል ተበዳይ ተጠራጥረው በአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ፖሊስ በግለሰቦቹ ላይ ባደረገው ፍተሻ 11ሺህ 2መቶ ሀሰተኛ የብር ኖት እንደተገኘባቸው እና ምርመራ የማጣራት ስራ እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በተለምዶ ጅንአድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ግለሰብ በሃሰተኛ ባለ 2መቶ የብር ኖት ባለ25 ብር የሞባይል ካርድ ለመግዛት ወደ ሱቅ ከሄደ በኋላ ሃሰተኛ ብሩን ሰጥቶ ካርዱን ሲቀበል ባለ ሱቋ ግለሰብ የተቀበለችው ገንዘብ ስላጠራጠራት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት በሰጠችው ጥቆማ እጅ ከፍንጅ ተይዞ በተደረገበት ፍተሻ 3ሺ 6 መቶ ሃሰተኛ የብር ኖት ተገኝቶበታል፡፡

ሃሰተኛ የገንዘብ ዝውውር በሀገር ኢኮኖሚ እድገት እና በህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ከራሳቸው ጥቅም አሳንሰው በማየት ወንጀሉን የሚፈፅሙ ግለሰቦች በተለይም የበዓላት መዳረሻ ወቅቶች ላይ የሚፈጠረውን የገበያ ግርግር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሐሰተኛ የብር ኖቶችን በስፋት ሊያሰራጩ ስለሚሞክሩ ህብረተሰቡ ግብይት ሲፈፅም ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ ወንጀሉን በመከላከል ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply