በሀቅ በአማራነት የተሰባሰበዉ ሀይል እና በሀቅ በኢትዮጵያዊነት የተሰባሰበዉ ሀይል በጋራ ሊወስዷቸዉ የሚገቡ ኢትዮጵያን የማዳን ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች ምንድን ናቸዉ? ———— ሸን…

በሀቅ በአማራነት የተሰባሰበዉ ሀይል እና በሀቅ በኢትዮጵያዊነት የተሰባሰበዉ ሀይል በጋራ ሊወስዷቸዉ የሚገቡ ኢትዮጵያን የማዳን ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች ምንድን ናቸዉ? ———— ሸንቁጥ አየለ ———– 1ኛ. እንደ ኢትዮጵያዊም ሆነ እንደ አማራ በሀገር ቤትም ሆነ በዉጭ ተበታትኖ የቆመዉ ሀይል ተናቦ መደራጀት ይገባል::ተናቦ መደራጀት ሲባል ግን ዝም ብሎ መቀላቀል አይደለም::መጀመሪያ በአማራ የተደራጀዉ ሀይል ሰብሰብ ብሎ መቆም::በኢትዮጵያዊነት የቆመዉም ሀይል ሰብሰብ ብሎ መቆም::ሰብሰብ ብሎ የቆሙት እነዚህ ሀይሎች ደግሞ እየተናበቡ የጋራ ጥረቶችን በፕሮጀክት ደረጃ ማከናወን:: ተናቦ ስራዎችን መከወን ወይም ተናቦ መደራጀት ሲባል ግን ቀላል አይደለም::በጋራ ሰልፍ ለመጥራት የማይችል ጠዋት ተነጋግሮ ከሰዓት ብኋላ የሚከዳዳ ሀይል ተናበብ… ስላልከዉ ብቻ ይናበባል ማለት አይደለም 2ኛ. በአማራ ማህበረሰብ ላይ እየተደረገ ያለዉ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲሁም በተዋህዶ ክርስቲያኖች ላይ የተከናወነዉን የዘር ማጥፋት ወንጀል በተቀናጀ እና በተናበበ መልክ ሁሉንም ወንጀለኞች ማለትም የብልጽግናን መንግስት:ኦነግን: ህዉሃትን እና ሌሎችንም ተዋንያዎች ባካተተ መልኩ በፍጥነት በአለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት ክሱ መቅረብ ይኖርበታል::ይሄንንም ማድረግ የሚቻለዉ ግን መናበብ ሲቻል እና በትብብር መስራት ሲቻል ነዉ::የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአለም አቀፍ ደረጃ የጀመረችዉን ክስ በማጠናከር እና አካታች እንዲሆን በማድረግ የዘር ማጥፋቱን ክስ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል::የተዋህዶን ሀይልና ጉልበት በዚህ መልክ ወደ ሀገር ማዳን ሂደቱ እንዲሳብ ማድረግ ቢቻል ትልቅ ድል ይሆናል:: 3ኛ. በአለም አቀፍ ደረጃ ተበታትነህ በየቋትህ ዉስጥ የምትገኝ ታጋይ ሁሉ ወደፊት መጥተህ:ተሰባስበህ:ተናበህ ስልጣን ለመረከብ በሚያስችል ህሳቤ ላይ ለመቆም ወስነህ የኢትዮጵያን ስነ መንግስት ለመረከብ መስማማት አለብህ::ሆኖም አንዳንዶቹ አሁንም እንኳን ስነ መንግስት እመረከብ ይቅርና ትግል የሚመስላቸዉ የሰፈራቸዉን ሰዎች እየሰበሰቡ ማህበረ ካቋቋሙ ብኋላ ሀሜት እና ምናምንቴ ወሬ መንዛት ነዉ::ላንዳንዶች ደግሞ ትግል የሚመስላቸዉ አስር እና መቶ ዶላር ወደ ሀገር ቤት መላክ ብቻ ነዉ::ድጋፍ በሀገር ቤት ለሚያደርጉ ሀይሎች ማድረግ ግማሹ የትግል ሂደት እጂ የትግሉ ፍጻሜ አይደለም::ሀገር ቤት ያለዉ ትግል በአንባገነኖች መፈናፈኛ ማጣቱነየታወቀ ሀገር ቤት ያሉትን ታጋዮች ብቻ እየተቹ በላክሁት ሳንቲም ለዉጥ አልመጣም ብሎ መማረር ነዉር ነዉ::ስለዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራጅቻለሁ የምትል ሁሉ ስነልቦናዊ አቋምህን አስተካክል:: የኢትዮጵያን ስነ መንግስት ለመረከብ የሚያስችልህ ህሳቤ ላይ ዉጣ::ይሄንንም ህሳቤ እዉን ለማድረግ እንዲቻል እና በመላዉ አለም የተበተነዉ ኢትዮጵያዊ እንዲደግፈዉ ለማድረግ እጅግ ብዙ ዉስብስብ ስራዎችን መከወን ይገባል:: 4ኛ.በሀገር ቤትም ሆነ በዉጭ ሀገር ያላችሁ ሁሉ አንዱ የጀመረዉን ጥረት ሌሎችችሁም አግዙ::ሁሉንም ወጥ እኔ ሽንኩርቱን ካልከተፍኩት:እኔ ቡኮዉን ካላቦካሁት አትበሉ::እርሾዉን በጥብጣችሁ አንድን ጥረት ያስጀመራችሁም ወገኖች ለሌሎች ሀይሎች ተሳትፎ ዋጋ በመስጠት አሳታፊነት ያለዉ አሰራር ብቻ ሳይሆን ብኋላ በመምጣት የተቀላቀሏችሁ ሌሎች ሀይሎችም የጥረቱ ባለቤት ነን ብለዉ እንዲያስቡ የሚያስችል ሁኔታ ፍጠሩ:: 5ኛ. በተባበሩት መንግስታት እና በምዕራባዉያን መንግስታት ዘንድ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመር አለበት::አሁን ያለዉ መንግስት ኢትዮጵያዉያን የጅምላ የዘር ፍጅት ሲደረግባቸዉ የዜጎችን የመኖር መብት ማስጠብቅ ያልቻለ መሆኑን በማስረዳት አማራጭ ሀይልን እንዲደግፉ የሚያስችል ስራ መሰራት አለበት::በተለይም በአማራ ማህበረሰብ ላይ በየደቂቃዉ በወለጋ:በመተከል:በጉራፋርዳ:በወልቃይት እና በመላ ሀገሪቱ በዬደቂቃዉ እየተከናወነ ያለዉን የዘር ማጥፋት ወንጀል ማጋለጥ ይገባል:: 6ኛ. አዴፓ/ብአዴን ከሚባል ሀይል ጋር እየተርመጠመጣችሁ የአማራ ብሄረተኛ ነን: ለአማራ ህዝብ እየሰራን ነዉ የምትሉ ብሎም በዉጭም በዉስጥም የአማራ ህዝብ እንዳይደራጅ እና ሚስጢር የሚጠብቅ አስራር እንዳይኖረዉ ለኦነግ/ኦህዴድ መረጃ የምታቀብሉ ህሙማን እራሳችሁን መርምሩ::የምትፈወሱበት መንገድ ግን በራሳችሁ እንዳልሆነ ይታወቃል::ስለሆነም እዉነተኛ የሆናችሁ አማሮች ከነዚህ መሰል አስመሳዮች እራሳችሁን ጠብቁ::የሰፈሬ ልጅ ነዉ: የወረዳዬ ልጅ ነዉ:የክፍለሀጌሬ ሰዉ ነዉ የሚለዉን ድኩም ሀሳብ እርሱት::ትግል መርህ ይፈልጋል::በመርህ መፋታተና በመርህ መራመድ የማይችል ትግል ብዙ ዋጋ ያስከፍላል:: 7ኛ. የአማራን ህዝብ ፈጽሞ ማዳን የሚቻለዉ ኢትዮጵያን ፈጽሞ ማዳን ሲቻል ነዉ::ኢትዮጵያን ፈጽሞ ለማዳን ደግሞ የኢትዮጵያን ስልጣነ መንበር መቆጣጠር ብቸኛዉ መፍተሄ ነዉ::ሆኖም አንዳንድ አስመሳይ የብአዴን ቅጥረኞች የአማራዉ አጠቃላይ ሀይል ወያኔ አማራ ክልል የሚለዉ ላይ ብቻ እንዲወሰን እና ኢትዮጵያን በባለቤትነት እንዳይጠይቅ የማደናበሪያ ፕሮፖጋንዳዎችን በመርጨት ህዝቡን ግራ እያጋቡ ነዉ::ይሄን አይነቱን ፕሮፖጋንዳ ማክሸፍ እና ትክክለኛዉን ሀሳብ ከማራመድ አትፍሩ:: 8ኛ. የኢትዮጵያን መንበረ ስልጣን ለመቆጣጠር ሌሎች ነገዶችን ማስተባበር:ማግባባት እና እዉነተኛ የኢትዮጵያዊነት ሀይሉን በጋራ ማሰለፍ ቁልፍ ስትራቴጅ ነዉ::ስለዚህ እዉነተኛ የአማራ ሀይሎች በፍጥነት በመጀመሪያ እራሳችሁን አሰባስባችሁ እና አናባችሁ ሌሎችን ወደ ማስተባበር ብሎም ወደ መተባበር መሄድ እንዳለባችሁ አትዘንጉ::ማስተባብር እና መተባበር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ነዉ::ድብረብርሃን ላይ አይንን ተክሎ:ወይም ባህርዳር ላይ ህልም ቆዝሞ ወይም ደግሞ ጎንደር ላይ ራዕይን አጠንጥኖ አለዚያም ደሴን ብቻ አልሞ አጠቃላይ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ብሎም የኢትዮጵያን ስነ መንግስት መረከብ አይቻልም::የኢትዮጵያን ስነ መንግስት ለመረከብ የኢትዮጵያ ስነመንግስታዊ ስሪቱ የቆመበት ቦታ ላይ አይንንም:ልብንም:መንፈስንም:ሀይልንም:ራዕዬንም : ህልምንም ማኖር ያስፈልጋል::የሚኒልክ ቤተ መንግስትን ላይ:: በተመሳሳይም በሀቅ በኢትዮጵያዊነት የተሰባሰባችሁ ሀይሎች እራሳችሁን በማሰባሰብ ከአማራ ሀይል :ሀገር እንዲኖራቸዉ ከሚፈልጉ በልዩ ልዩ ነገድ ስም ከተደራጁ ሀይሎችም ጋር የምትናበቡበትን ስልት መንደፍ ይጠበቅባችኋል::ይሄም ማለት እራሳችሁን ከመኮፈስ በማዉጣት የነገድ ድርጅቶች ጋር መተባበር እንዲሁም ማስተባበር የሚለዉን ህሳቤ መተግባርን ሁሉ ያካተተ ነዉ:: 9ኛ. የዘር ፍጅት እየተከናወነበት ያለዉን የአማራን ማህበረሰብ አሁንም በሩቅ ገጠሮች: በቆላማ ስፍራዎች:ለተደራሽነት አስቸጋሪ በሆኑ ቀበሌዎች መድረስ እና ማንቃት አልተቻለም::ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ስራ ይጠይቃል::አማራዉ ከዳር እስከዳር የነቃ እንደሆነ : ነቅቶም የተደራጀ እንደሆነ መደራጀቱም እጁ ላይ የሚያገኘዉን ማንኛዉንም የተፈጥሮ ጸጋ ሁሉ እራሱን ለማስከበር በሚያስችለዉ ደረጃ እንዲገነዘበዉ የተደረገ እንደሆነ መላዉ ኢትዮጵያን በአንድ ቀን ሌሊት ሊያነቃንቃት ይችላል::ይሄም ሆኖ ታዲያ የአማራዉን የማንቃት ስራ ከመላዉ ኢትዮጵያ ህዝብ የማንቃት ስራ ጋር ማስተሳሰር :ኢትዮጵያዉያን ሁሉ የጋራ ህልም እና ራዕይ እንዲያልሙ ማድረግ እና ለጋራ ግብ እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ስራም አብሮ መሰራት የግድ አለበት:: 10ኛ. በመጨረሻም ፈጽሞ መዳን ያለባት ኢትዮጵያ ነች::ኢትዮጵያም ፈጽማ ስትድን ሁሉም ይድናል::ሁሉም ኢትዮጵያዊ ረፍት ያገኛል::ኢትዮጵያን ማዳን ሲቻልም የጎሳ ፖለቲካን በህግ ማገድ:የጎሳ አከላለልን ማፍረስ እና በተሻለ አከላለል መተካት: አሁን ያለዉን የጎሳ ህገመንግስት በፍጹም ኢትዮጵያዊ ህገመንግስት መቀዬር ይገባል::ይሄን የጋራ መዳረሻ ራዕይ እና ግብ ገና ከመነሻዉ ሁሉም ሀይል ተቀብሎት እንዲነሳ የማድረግ ስራም መሰራት አለበት::አሁን በጎሳ የተደራጁ ልዩ ልዩ ሀይሎችም ኢትዮጵያን ማዳን በሚቻልበት ወቅት የጎሳ ድርጅታቸዉን አክስመዉ ወደ ሀገራዊ ፖለቲካ ከፍ እንዲሉ ከመነሻዉ የስምምነት የሀሳብ አምድ ላይ መድረስ ይገባል::ኢትዮጵያዉያን ሀገር እንዲኖራቸዉ ከፈለጉ ያለዉ ብቸኛዉ መፍትሄ እና አማራጭ የጎሳ ፖለቲካን ስሩን በህግ ማገድ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡን ነቅሎ መጣል ወሳኝ ነዉ:: እንግዲህ በዚህ ነገር ዉስጥ ሁሉ ኢትዮጵያን ለማዳን እግዚአብሄር ይቅደም::እግዚአብሄርም ህዝቡን ይምራ! ኢትዮጵያም ፈጽሞ ትድናለች ! አሜን !!!

Source: Link to the Post

Leave a Reply