በሀገሪቱ ያሉ ልዩነቶች በምክክር ሂደት ብቻ እንደሚፈቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

በማንኛውም አካል የሚነሱ ጥያቄዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ሊፈቱ ይገባል ሲል የጋራ ምክር ቤቱ ለኢትዮ ኤፍኤም አስታውቋል፡፡

በተለይም ከሰሞኑ በራያ እንደ አዲስ ያገረሸው ውጥረትን ተከትሎ እየታየ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ስለመሆኑ ተነስቷል፡፡

በትግራይ እና አማራ አካባቢዎች ላይ እየተከሰተ ያለውን ውጥረት በተመለከተ ለጣቢያችን አስተያየታቸውን የሰጡን በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ፈይሰል አብዱላዚዝ ካሳለፍነው ሁለት ዓመት ጦርነት ትምህርት ልንወስድ ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ፖለቲካ የጋራ ምክር ቤትም ሆነ እንደ ፓርቲ በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ ውዝግቦች ያሳስቡናል የሚሉት አቶ ፈይሰል አላግባባ ያሉ ጥያቄዎችን ወደ ምክክር ኮሚሽን በመውሰድ በውይይት መፍትሄ እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ዜጎች እንዳይፈናቀሉ እና እንዳይገደሉ ከምንም በፊት ስምምነት ላይ መደረስ ያስፈልጋል ሲሉ ለጣብያችን ተናግረዋል፡፡

ሌላው በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ምህዳር መስፋት አለበት ብለን እናምናለን ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መታሰር አለበት ብለን አናስብም ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ሲባል ወንጀል የሰራውም ለምን ታሠረ የሚል ሀሳብ መኖር የለበትም ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደ ፖለቲካ የጋራ ምክር ቤት በዚህ ወቅት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ይታያል የሚሉት አቶ ፈይሰል ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ከመንግስትም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ክፍተቶች አሉ ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን ሰብሰብ ብለው መንግስትን ወደ የመሞገት ሊኖር ይገባል ሲሉ ከጣብያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

አቤል ደጀኔ
ሚያዚያ 11ቀን 2016 ዓ.ም

ኤትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጲያዊያን

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply