በሀገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው መያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው አመራሮችና የጦር መኮንኖች መካከል 15ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/…

በሀገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው መያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው አመራሮችና የጦር መኮንኖች መካከል 15ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 27 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው መያዣ ትዕዛዝ ከአወጣባቸው ከ300 በላይ አመራሮችና የጦር መኮንኖች መካከል 15ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን እና አምስቱ ደግሞ በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት እርምጃ እንደተወሰደባቸው መረጋገጡን አስታውቋል። አሁንም በየጥሻውና በየጉድጓዱ የተደበቁትን በሀገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው መያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸው አመራሮችና የጦር መኮንኖች የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በማደን ላይ እንደሚገኝ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሚያካሄዱት የህግ ማስከበር ዘመቻ በጁንታው የህወሃት ቡድን ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመሳተፍ የጥፋት ስራው አካል ናቸው ብሎ በጠረጠራቸው ከ300 በላይ ከፍተኛ አመራሮችና የጦር መኮንኖች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት መውጣቱ ይታወቃል። በዚህም እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ከፍተኛ መኮንኖች መካከል፡- 1. ሜ/ጀኔራል ገ/መድህን ፈቃዱ ሀይሉ 2. ሜ/ጀኔራል ይዳው ገ/መድህን 3. ብ/ጀኔራል ገ/ህይወት ሲስኖስ ገብሩ 4. ብ/ጄኔራል ኢንሱ እጃጆ እራሾ 5. ብ/ጄኔራል ፍስሃ ገ/ስላሴ 6. ኮ/ል ደሳለኝ አበበ ተስፋዬ 7. ኮ/ል እያሱ ነጋሽ ተሰማ 8. ኮ/ል መብራቱ ተድላ ወ/ሚካኤል 9. ኮ/ል ባራኪ ጠማሎው ገብሩ 10. ኮ/ል ሀይላይ መዝገብ ማሾ 11. ኮ/ል ፍሰኃ ግደይ ወ/ማርያም 12. ሌ/ኮ/ል ሙዘይ ተሰማ ስዩም 13. ሌ/ኮ/ል ፍሰሃ በየነ ገ/ኪዳን 14. ሌ/ኮ/ል ምሩጽ ወ/አረጋይ ገ/መስቀል 15. ሌ/ኮ/ል ምሩጽ በርሄ አበራ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸዉ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለም የመያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው 81 የህወሀት ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ዶ/ር አዲስአለም ባሌማ የተያዘ መሆኑ ይታወቃል። የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ባካሄዱት የተቀናጀ የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በተካሄደው የምርመራ ስራ እንደተጣራው እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል፡- 1. ኮ/ል ተስፋዬ ገ/መድህን 2. ኮ/ል የማነ ገ/ሚካኤል 3. ሌ/ኮ/ል ሀዲሽ ገ/ጻዲቅ 4. ኮ/ል ማዕሾ 5. ኮ/ል አለም ገ/መድህን የተባሉት እንደሚገኙበት ተረጋግጧል። የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት ቀሪ ያልተያዙ የጦር መኮንኖችንና የህወሀት አመራሮችን ከየተደበቁበት ጥሻ፣ ዋሻ እና የሀይማኖት ስፍራዎች በማደንና በመልቀም ለህግ ለማቅረብ ቀን ተሌት እየሰራ እንደሚገኝም ፖሊስ አስታውቋል። የጁንታው የህወሀት አመራሮች በውጊያ ከተሸነፉ በኃላ ራሳቸውን ካለባበስ ጀምሮ በመቀያየር ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ ፖሊስ መረጃው እንደደረሰውም ነው የተገለፀው። የትግራይ ክልል ህዝብ ህግ ለማስከበር በተደረገው ዘመቻ እስከዛሬ ላደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ኮሚሽኑ ምስጋና እያቀረበ ያልተያዙትን ተፈላጊዎች ከተደበቁበት ቦታ ይዞ ለህግ ለማቅረብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከፖሊስ አባላት ጎን በመቆም እና አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply