በሃላፊነት ቦታ የተቀመጡ ሰዎች ከከፋፋይ ንግግሮችና መግለጫዎች እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አሳሰበ፡፡ኢትዮጵያ አስከፊ ከሆነ ጦርነት ወጥታ ሕዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ…

በሃላፊነት ቦታ የተቀመጡ ሰዎች ከከፋፋይ ንግግሮችና መግለጫዎች እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

ኢትዮጵያ አስከፊ ከሆነ ጦርነት ወጥታ ሕዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ በጀመረበት በዚህ ወቅት በሃላፊነት ቦታ የተቀመጡ ግለሰቦች የህዝቦችን አብሮነት በማስቀደም ተጨማሪ ግጭትና መራራቅ እንዳይፈጠር ተግተው ሊሰሩ በሚገባበት ሰዓት፣ አንዱን ሕዝብ መጤ ሌላውን ነባር፤ አንዱን ብሔር ፀረ ሰላም ሌላውን የሰላም ዘብ፤ አንዱን የኃይማኖት ተከታይ ሰላማዊ ሌላውን አመፀኛ አድርጎ መሳልና መከፋፈል በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም ብሏል ም/ቤቱ፡፡

መገናኛ ብዙኃንም በዘገባዎቻቸው ማናቸውንም የህብረተሰብ ክፍል በዘር፣ በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካዊ አስተሳሰብን መሠረት በማድረግ የሚሰጥ/የሚነገር/ ጥላቻን የሚያበረታታ፤ ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ የአደባባይ መግለጫዎችን ፤ ንቀትን ወይም መገለልን ሊፈጥር የሚችል ቋንቋን የሚጠቀሙ እንግዶችን ከመጋበዝ እና ከፋፋይ መግለጫዎችንም በማህበራዊ ሚዲያ ጭምር ከማሰራጨት መቆጠብ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት እንዳለው፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘመናት አብሮ በኖረው ህዝብ መሀል አንድነትን የሚሸረሽር፤እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያይ የሚያደርግ ከፋፋይ የሆኑ ንግግሮች፤ መግለጫዎችና ሀሳቦች በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት በስፋት እየተሰራጨ ነው ብሏል፡፡

አንዳንዶቹ አሉታዊ ይዘት ያላቸው ንግግሮችና መግለጫዎች በመንግስት ባለስልጣናት፤በፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች፤ በሀይማኖት ሰባኪያንና በምሑራን መደረጉን አስታውሶ መገናኛ ብዙኃን በሕጉ አግባብ ሙያዊ ነፃነታቸውን ተጠቅመው ስራቸውን ከፍ ባለ የኃላፊነት ደረጃ ማከናወን እንደሚኖርባቸው ገልጿል፡፡

ንግግሮቹ በማንም ይነገሩ በማን ያለፉ ቁስሎችን ከሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን ከሚያነግሡ፣ ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ የሚያደርጉና፣ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መልዕክቶችን ከማሰራጨታቸው በፊት አስፈላጊውን የአርትኦት ስራ ሊሰሩባቸው ይገባልም ብሏል፡፡

በመሆኑም የፕሬስ ነፃነት ከሙያ ስነ ምግባር ጋር የተቆራኘ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን የጋራ ሰላምንና ወዳጅነትን ለማሳደግ እጅግ የተለየ ኃላፊነት እንዳለባቸው ማስታወስ ይገባቸዋል ነው ያለው፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም

ለተጨማሪ መረጃዎች የቴሌግራምና የዩቲዩብ ቻናሎቻችንን ይቀላቀሉ!
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast

ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 6321 ላይ ይላኩልን።
ከኛ ጋር ስለሆናችሁ ከልብ እናመሰግናለን

Source: Link to the Post

Leave a Reply