በህወሓት ውስጥ ያለ ቡድን ለውጊያ ያሰለፈን በግዳጅ ነው – በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂዎች

በህወሓት ውስጥ ያለ ቡድን ለውጊያ ያሰለፈን በግዳጅ ነው – በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂዎች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህወሓት ውስጥ ያለ ቡድን ለውጊያ ካሰለፋቸው የክልሉ ልዩ ሃይልና ሚሊሻዎች መካከል በርካቶቹ በግዳጅ ወደ ጦርነት መግባታቸውን በሀገር መከላከያ ሃይል በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂዎች ተናገሩ።

የህወሓት ጁንታ በትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ሰራዊቱ ሀገር የማዳን ተልዕኮ ተሰጥቶት በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ስራ ላይ ይገኛል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት በምድርና በአየር የዘመቻ ስራውን እያከናወነ ሲሆን የተለያዩ ቦታዎችንና ለውጊያ የተሰለፉ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ላይ መሆኑ ይታወቃል።

መከላከያ ሰራዊቱ በቁጥጥር ስር እያዋላቸው ካሉት ታጣቂዎች ውስጥ አብዛኞቹ እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ታዳጊዎች ናቸው።

ከታጣቂዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደገለጹት፤ ህወሓት ውስጥ ያሉ አመራሮች ልጆቻቸውን በውጭ ሀገር እያስተማሩ የደሃ ልጆችን በግዳጅ ለውጊያ በማሰለፍ ህይወታቸውን እንዲያጡ እያደረጉ ነው።

ለውጊያው እንዲሰለፉ ከተደረጉት የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻዎች መካከል በርካቶቹ በህወሓት ተገደው ወደ ውጊያ የገቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

የህወሓት ቡድን የሚያደርገውን የግዳጅ ዘመቻ ያልተቀበለ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እስከሞት የሚደርስ ቅጣት የሚፈፀምበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ ህወሓት ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ የሚፈፅመው ተግባር መቆም እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በፅንፈኛው የህወሃት ቡድን ትእዛዝ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሃይል ላይ የክልሉ ልዩ ሃይል ጥቃት እንዲፈፅም መደረጉም ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።

በጦርነቱ በሀገር መከላከያ ሃይል በቁጥጥር ስር የዋሉት ታጣቂዎች እጃቸውን ከሰጡ በኋላ የደረሰባቸው ችግር እንደሌለና በጥሩ ሁኔታ መያዛቸውን አስረድተዋል።

ጦርነቱን በሚመለከት በህወሓት አመራሮች የተነገራቸው ሁሉ የተሳሳተና ሀገርን የመካድ ድርጊት መሆኑን ገልጸው፤ በርካቶች ባገኙት አጋጣሚ ህወሓትን እየከዱ መሆኑን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

The post በህወሓት ውስጥ ያለ ቡድን ለውጊያ ያሰለፈን በግዳጅ ነው – በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂዎች appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply