በህወኃት ውስጥ ባለ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት አሳፈሪ ተግባር ነው – አቶ አወል አርባ

በህወኃት ውስጥ ባለ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት አሳፈሪ ተግባር ነው – አቶ አወል አርባ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህወኃት ውስጥ ባለ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መሰተዳደረ አቶ አወል አርባ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳደሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፤ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በሀገርና በህዝብ ላይ የተቃጣ እኩይ ተግባር ነው።

ጥቃቱን ተከትሎ መንግስት ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር እየወሰደ የሚገኘው እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል እንዲጠናቀቅ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አሰታውቀዋል።

አቶ አወል በመግለጫቸው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ባለፉት ሁለት አስርት ቁርና ሐሩር ሳይበግረው የወገኑን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ የህይወት መስዋዕትነት መክፈሉን አስታውሰዋል።

ይህን መስዋዕትን ከቡድንና ግል ጥቅም አሳንሶ የተረዳው ህወሃት ውስጥ ያለው ቡድን የፈጸመው ጥቃት አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር ነው ብለዋል።

ቡድኑ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለህዝብ ደህንነት ደንታ እንደሌለው በእኩይ ተግባሩ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

“በተለይም አገራችን ከህዳሴው ግድቡ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ ባለችበትና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በቆሙበት ወቅት በመከላከያ ላይ ጥቃት መፈጸም የአገር ክህደት ነው” ብለዋል።

ጥቃቱ በግልጽ አገርን የማፈረስ ዓላማ ያለው እኩይ ተግባር በመሆኑ የክልሉ መንግስትና ህዝብ አጥብቆ እንደሚያወግዝ ርዕሰ መሰተዳድሩ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሀገሪቱን ደህንነትና ህገመንግስቱን ከጥቃት ለመጠበቅ በሚወስደው ማናቸውንም እርምጃ ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ የትግራይ ህዝብ የቆየ ሀገር ወዳድነቱን ጠብቆ ውድ ልጆቹ ለጥቂቶች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

The post በህወኃት ውስጥ ባለ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት አሳፈሪ ተግባር ነው – አቶ አወል አርባ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply