በህገወጥ የሃዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለጠቆመ እስከ 25 ሺሕ ብር ወረታ እንደሚከፈል ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

አርብ መስከረም 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በህገወጥ የሃዋላ የውጭ አገራት የተሰማሩ አካላትን ለጠቆመ እስከ 25 ሺሕ ብር ወረታ እንደሚከፈል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጥቁር ገበያ ቁጥጥርና አስተዳደራዊ እርምጃ፤የዋጋ ግሽፈትና ህገወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ግብይትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
የባንኩ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፤ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ በማድረግ በኢትዮጵያ ውጤት እየተመዘገ ቢገኝም የዋጋ ግሽፈትና ምርታማነትን ከማሳደግ የንግድ ስርዓቱን ከማዘመን አንፃር ውስንነት እንዳለ ተናግረዋል።
ህገወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ምንዛሬም ለዋጋ ግሽፈትና ንግድ ስርዓቱ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተናገሩት ገዢው፤ የሃዋላ አገልግሎት ሥራ የሚሰሩ አካላት ላይ አስተዳራዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ህገወጥ የሃዋላ ሥራ የሚሰሩ አካላት ህጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸው አሉ፤ ህጋዊ እስከሆኑ ድረስም መበረታት አለባቸው፤ኢትዮጵያም የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ እያደረጉ ነው ብለዋል።
ነገር ግን የውጭ አገራት ገንዘብ ምንዛሬ የሃዋላ አገልግሎት ፈቃድ ወስደው ከባንክ ውጭ የምንዛሬ አገልግሎት በመስጠት ዶላር ዋጋ ምንዛሬ በፍጥነት እንዲያድግ እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ምርት አለመመጣጠንም ለዶላር ምንዛሬ የራሱ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑንም በመግለጽ፤ የውጭ አገራት ገንዘብን በጥቁር ገበያ ህገወጥ የምንዛሬ ሃዋላ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ 391 ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው እንዲዘጋ መደረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያንም በግለሰብ ደረጃ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ለድርጅቶች ደግሞ ከ200 ሺሕ ብር በላይ ቤት ውስጥ ማስቀመጥ የተከለከለ መሆኑን መገንዘብ እንደሚኖርባቸውም ዶክተር ይናገር ተናግረዋል።
ገንዘብ በባንክ መቀመጥ እንዳለበትና የግብይት ስርዓትም በባንክ ማካሄድ እንደሚቻል ገልጸው መመሪያው ከሚፈቅደው የገንዘብ መጠን በላይ አስቀምጦ የተገኘን አካል የጠቆመ ግለሰብ 15 በመቶ የወረታ ክፍያ እንደሚፈጸም ገልጸዋል።
በውጭ አገራት ገንዘብ ግብይት መፈጸምም ሆነ በህገወጥ መንገድ ይዞ መገኘት እንደማይቻል ተናግረዋል።
ወርቅን በህገወጥ መልኩ ቤት ውስጥ አከማችቶ እንደማይቻልና በህገወጥ መልኩ ወርቅን ያከማቸ ግለሰብ ለጠቆመም ግለሰብ ባንኩ በወቅቱ ባለው ግብይት የ15 በመቶ ወረታ ይከፈለዋል ብለዋል።
በህገወጥ የሃዋላ የውጭ አገራት የተሰማሩ አካላትን ለጠቆመም እስከ 25 ሺሕ ብር ወረታ እንደሚከፈልም የጠቆሙት የባንኩ ገዥ፤ በህገወጥ ገንዘብ ህትመት የተሰማሩ አካላትን ያጋለጠም ከ20 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር ወረታ እንደሚከፈለው ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

The post በህገወጥ የሃዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለጠቆመ እስከ 25 ሺሕ ብር ወረታ እንደሚከፈል ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply