በህገ ወጦች ላይ ምህረት የለሽ እርምጃ እንወስዳለን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2014 በህገ ወጦች ላይ ምህረት የለሽ እርምጃ እንወስዳለን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቋራጭ ለመክበር በሚሞክሩ አካላት ላይ ምህረት የለሽ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ከንቲባዋ በከተማዋ ዘይትን ጨምሮ በሌሎች ሸቀጦች ላይ ዋጋ የሚያስጨምር ምንም አይነት ምክንያት የለም በማለት ተናግረዋል፡፡

የምርት እጥረት ቢኖርም እንኳ ያለውን ምርት ግን በትክክል ለህብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ያቋቋመው ግብረሃይል ባደረገው እንቅስቃሴ ዘይት ተጭኖ ወደ ሌላ ቦታ ለማሸሽ የሚደረጉ ጥረቶች እንዲከሽፉ መደረጋቸውንም ገልጸዋል። ሕዝቡ ሕገ-ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን ማጋለጥ እንደሚገባው ገልጸው ያልተገባ ጭማሪ በሚያደርጉት አካላት እርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ለሸማች ማህበራት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መድበን ምርቱን ወደ ገበያ ለማስገባት አቅርበናል፤ በትክክል ወደ ሕዝቡ ስለመድረሱ ደግሞ መከታተል ይኖርብናል ብለዋል። ከሌሎች ፕሮጀክቶች ቀንሰን ከፍተኛ በጀት የመደብነው ሕዝቡ ጋር እንዲደርስ ነው፤ ማንም ባቋራጭ መንገድ እንዲከብርበት አይደለም፤ በዚህ መንገድ ለሚመጣ ማንኛውም እጥረት ምህረት የለሽ እርምጃ እንወስድበታለን ሲሉ ለሸማቾች ማህበራት መልዕክት አስተላልፈዋል። ሕዝቡ ለአገሩ ቅድሚያ ሰጥቶ አስተዋፅኦ አበርክቷል ያሉት ከንቲባዋ ከዚህ ህዝብ መዝረፍ ከወንጀልም በላይ ወንጀል ነው ማለታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply