በህጻናት ምግብ ላይ ምን ያህል ጨው መጨመር ይገባል?የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ  እንደሚያመላክተው ጨቅላ ህጻናት ከ 6 ወራት በኋላ ተጨማሪ ምግብ መጀመር እንዳለባቸው ነው፡፡ ነገር ግን በተለ…

በህጻናት ምግብ ላይ ምን ያህል ጨው መጨመር ይገባል?

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ  እንደሚያመላክተው ጨቅላ ህጻናት ከ 6 ወራት በኋላ ተጨማሪ ምግብ መጀመር እንዳለባቸው ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ህጻናት ከ 4 ወር በኋላ ተጨማሪ ምግብ  የሚጀምሩበት ሁኔታ  መኖሩ ተመላክቷል፡፡

ህጻናት መቼ ጨው መጀመር እንዳለባቸው እና በምን ያህል መጠን ሊሰጣቸው እንደሚገባ የነገሩን፤ የህጻናት ሀኪም ዶክተር ማህሌት አድማሱ ናቸው፡፡

ጨቅላ ህጻናት ለጤናቸው የሚጠቅማቸውን እና በሽታ ለመከላከል የሚረዳቸውን ንጥረ ነገር በእናት ጡት ውስጥ ስለሚያገኙ እስከ 6 ወራት ድረስ የእናት ጡት ብቻ እንዲጠቡ ይመከራል ብለዋል፡፡

ለጨቅላ ህጻናት ወይም ለታዳጊዎች እስከ 2 ዓመታቸው ድረስ አመጋገባቸው በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ ባለሞያዋ ተናግረዋል፡፡ ጥንቃቄ መደረጉ ለህጻናቱ አካላዊ እና አእምሮ እድገታቸውን ለመጨመር እና ለበሽታ የመጋለጥ እድልን ለመቀነስ እንደሚረዳ ተነግሯል፡፡

ከ6 ወራት እስከ 1 ዓመት ድረስ በህጻናት ምግብ ላይ ምንም አይነት ጨው እና ስኳር መጨመር እንደማይገባ ዶክተር ማህሌት ተናግረዋል፡፡ 

የጨው ይዘት በህጻናት ምግብ ላይ ማብዛት የሚያስከትለው ጉዳት

•  ከመጠን ያለፈ ሶዲየም በምግብ ላይ መጠቀም ከሚያስፈልገው በላይ ፈሳሽ በሰውነት ውስጥ እንዲጠራቀም ያደርጋል ተብሏል፡፡

•  የኩላሊት መዳከም እና ግፊት ያስከትላል፡፡

•  በህጻናቱ ላይ የጨው ይዘት የበዛባቸው ምግቦች የመመገብ ልማድን ያመጣል፡፡

ለጨቅላ ህጻናት ወይም ለታዳጊዎች በምግባቸው ላይ ምን ያህል የጨው መጠን ሊጨመር ይገባል?

      •ከ1 እስከ 3 ዓመት ድረስ ያሉ ህጻናት በቀን ውስጥ በሚመገቡት ምግብ ውስጥ ከ 1 ሺህ 500 ሚሊ ግራም በላይ ሶዲየም ወደ ሰውነት ውስጥ መግባት የለበትም ተብሏል፡፡

      •ከ4 እስከ 8 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ  የሚገኙ ህጻናት ከ1 ሺህ 9 መቶ ሚሊ ግራም በታች ሶዲየም መሆን አለበት።

     •ከ9 እስከ 14 ዓመት ላሉ ታዳጊዎች በሚመገቡት ምግብ ውስጥ ከ2 ሺህ 200 ሚሊ ግራም  በታች ሶዲየምን መጠቀም ይገባል፡፡ 

    •ከ14 ዓመት በላይ የእድሜ ክልል ላሉ ከ2ሺ 300 ሚሊግራም ሶድየም በታች በምግብ ውስጥ መጠቀም ይገባል ተብሏል፡፡

የታሸጉ ምግቦችን አዘውትሮ መጠቀም በህጻናቱ ጤና ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ተብሏል፡፡ ከ1 እስከ 3 ዓመት ድረስ ያሉ ህጻናት በቀን ከ አንድ የሻይ ማንኪያ  ጨው 3 አራተኛውን ብቻ መጠቀም እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

እንዲሁም  ከ18 ዓመት በላይ የሚሆኑ ሰዎችም በቀን ውስጥ በምግብ ውስጥ አንድ የሻይ ማንኪያ ጨው ብቻ መጠቀም እንደሚገባ ተነግሯል።

በእሌኒ ግዛቸው

ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply