በሆሮ ጉድሩ ታጣቂዎች ነዋሪዎችን እና የሚሊሻ አባላትን መግደላቸውን ተገለጸ የአማራ ሚዲያ ማዕከል መስከረም 15 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስ…

በሆሮ ጉድሩ ታጣቂዎች ነዋሪዎችን እና የሚሊሻ አባላትን መግደላቸውን ተገለጸ የአማራ ሚዲያ ማዕከል መስከረም 15 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በሰላማዊ ነዋሪዎች እና በአካባቢው የሚሊሻ አባላት ላይ ግድያ መፈጸማቸውን መንግሥት አስታወቀ። በሽብርተኝነት የተፈረጀውና መንግሥት ሸኔ በማለት የሚጠራው ይህ ቡድን በምዕራብ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተከታታይ በሚፈጸሙ እና በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ግድያዎች ይከሰሳል። ባለፉት ቀናት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ውስጥ ታጣቂው ቡድን ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን፣ በተከታታይ ቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 14/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ታጣቂው ቡድን በዞኑ ውስጥ “በንጹሃን ዜጎች እና በአካባቢው የሚሊሻ አባላት ላይ ግድያን ፈጽሟል” ያለ ሲሆን ስለተገደሉት ሰዎች ብዛት ግን ያለው ነገር የለም። የተለያዩ ምንጮች ግን በጥቃቱ የተገደሉትን ሰዎች አሃዝ በአስራዎቹ ውስጥ የሚያስቀምጡት ሲሆን፣ ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም። በአካባቢው በታጣቂው ቡድን አባላት ላይ የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው ያለው መግለጫው “በንጹሃን ላይ የሚፈጸመው የጭካኔ ድርጊት እጅግ አሳዛኝ ነው” ብሏል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ታጣቂዎቹ ፈጽመውታል ስለተባለው ስለዚህ ጥቃት አስካሁን ያለው ነገር የለም። የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ቡድኑ በስፋት በሚንቀሳቀስባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በፀጥታ ኃይሎችና በሕዝቡ ቅንጅት እርምጃ እንደተወሰደበት ያመለከተው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መግለጫ “እየተበተነ ወደ ሆሮ ጉድሩ ጃርደጋ ጃርቴ አካባቢ ሲሸሽ ነበር” ብሏል። ጨምሮም ቡድኑ በዚህ ሳምንት ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የፈጸመው በፀጥታ ኃይሎች “የተገደለበትን የአካባቢው ታጣቂዎች አዛዥ እና ሌሎች አባላቱን ደም ለመበቀል” እና በቀጣይ ሳምንት የሚከበሩ “የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትን ለማወክ ነው” ብሏል። አሁን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሞበታል የተባለውን የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞንን ጨምሮ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ይንቀሳቀስባቸዋል በሚባሉት የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት ሰላማዊ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣንት እንዲሁም ተቋማት ጥቃት ሲፈጸምባቸው ቆይቷል። በተለይ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በአካባቢው ነዋሪ በሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶች መፈጸማቸው ይታወሳል። መንግሥት እና ከጥቃቶቹ የተረፉ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የበርካቶችን ሕይወት ለቀጠፉት ጥቃቶች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቡድኑ ግን ድርጊቱን ሲያስተባብብል ቆይቷል። በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከተገደሉትና ጉዳት ከደረሰባቸው ነዋሪዎች ባሻገር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ለበርካታ ነዋሪዎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ በታጣቂዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች በእጅጉ እንዳሰሳሰቡት ከሳምንታት በፊት ባወጣው መግለጫ ማመልከቱ ይታወሳል። ኮሚሽኑ እንዳለው ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፤ ከ70 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጿ ነበር። እንዲሁም ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪው ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ባወጣው መግለጫ ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች ሲገደሉ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ለመከላከል በቂ ጥበቃ አላደረጉም ሲል ወቅሶ ነበር። ምንጭ ቢቢሲ

Source: Link to the Post

Leave a Reply