በሆሮ ጉድሮ ዞን ሻምቡ ከስብሰባ ቆይተው ሲመለሱ 3 አጃቢዎቻቸው ተለይተው በኦነግ ሸኔ የተገደሉባቸው 2 የወረዳ አመራሮች ታሰሩ

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሮ ዞን ሻምቡ ስብሰባ የቆዩት የአቢደንጎሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባዝኔ ኡርጅራ፣የወረዳው ህግና ፍትህ ሀላፊ አቶ አምሳሉና የወረዳው የፖሊስ አዛዥ ነጋሳ በ3 የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ታጅበው ወደ አቢደንጎሮ እያቀኑ ነበር፤ ህዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም ሻምቡ ስብሰባ ቆይተው ወደ አቢደንጎሮ ወረዳ ሲመለሱ ሆሮ አካባቢ በመኪና ላይ እያሉ በደፈጣ ላይ የነበረው ኦነግ ሸኔ በፈፀመው ጥቃት 3 አጃቢዎቻቸው ተለይተው ተገድለዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ፣የፖሊስ አዛዡና የህግና ፍትህ ሀላፊው 3ቱ አመራሮች ጉዳት ሳይደርስባቸው በህይወት ስለመትረፋቸው ነው ነዋሪዎች የተናገሩት። አመራሮችም በጫካ አደርን በሚል ህዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ አቢደንጎሮ ወረዳ ሲመለሱ አምሳሉ የተባሉት የወረዳው የህግና ፍትህ ሀላፊ እንዲሁም የፖሊስ አዛዥ ነጋሳ በልዩ ሀይል ታስረዋል፤ አቶ ባዝኔ ኡርጅራ ግን ታምሜያለሁ ብለው መተኛታቸው ነው የተገለፀው።

ጥያቄው መንገድ ላይ የመሸጉ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች አጃቢ ልዩ ሀይሎቹን ብቻ ነጥለው እንዴት ሊገድሉ ቻሉ? አመራሮች ከኦነግ ሸኔ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ተጠርጥረው ስለመታሰራቸው ነው ምንጮች የተናገሩት። በአቢደንጎሮ ወረዳ ቱሉጋና ቀበሌ ላይ ልዩ ሀይልም ሆነ መከላከያ ባለመመደቡ ቅሬታ እንዳላቸው የተናገሩት ነዋሪዎች ከሰሞኑ ውባንች ጫንጮ አካባቢ የኦነግ ሸኔ ስጋት አለ በመባሉ የፀጥታ አካል ወርዶ የአሰሳ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ነዋሪዎች የአቢደንጎሮ ወረዳ አስተዳዳሪን ጨምሮ በወረዳው ያሉ አንዳንድ አመራሮች ከኦነግ ሸኔ ጋር ይገናኛሉ የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ነበር፤ በተለይም ከወራት በፊት በእርሻ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአቢደንጎሮ አማራዎችን ከመሬት ባለቤትነት ውጭ ለማድረግ የተሄደበትን መንገድ አድሎአዊና ከቀያችን ለማፈናቀል የታቀደ ሲሉ መቃወማቸውና ቅሬታቸውንም እስከ ክልልና ፌደራል ድረስ ይዘው መቅረባቸው ይታወሳል። የሆሮ ጉድሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ መረጃ እንዲያጋሩን ያደረግነው ጥረት ስብሰባ ላይ ነኝ በማለታቸው እንዲሁም የኦሮሚያ ብልፅግና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ የሚጠራ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አስተያየታቸውን ለማካተት አልተቻለም።

Source: Link to the Post

Leave a Reply