“በሐምሌ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33 ነጥብ 5 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል”፦የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት

የምግብ የኢንዴክሱ ክፍሎች መጠነኛ መረጋጋት ያሳዩ ሲሆን፤ ምግብ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ላይ ጭማሪ ታይቷል

ማክሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በየወሩ የሚያወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ መሰረት፤ የሐምሌ ወር 2014 አጠቃላይ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት 33 ነጥብ 5 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን አስታውቋል።

ባሳለፍነው ሰኔ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 34 በመቶ ደርሶ የነበረ ሲሆን፤ በሐምሌ ወር 2014 ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር 2013 ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ መረጋጋትን በማሳየት 33 ነጥብ 5 ከመቶ ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ በላከው መረጃ ገልጿል።

በያዝነው ወር የምግብ የኢንዴክሱ ክፍሎች መጠነኛ መረጋጋት ያሳዩ ሲሆን፤ ምግብ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ላይ ግን ጭማሪ ታይቷልም ተብሏል፡፡

”ባለፉት 12 ወራት ጭማሪ የታየ ቢሆንም፤ ጭማሪው ከወር ወር በተመሳይ ሁኔታ የጨመረ በመሆኑ የዋጋ ግሽበቱ ከቁጥጥር ውጭ አልሆነም“ ያለው አገልግሎቱ፤ ለዚህም ዋጋን ለማረጋጋት የተወሰዱ እርምጆች የከፋ ጉዳት እንዳይርስ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አድርገዋል ብሏል።

ነገር ግን በያዝነው ወርም በእህሎችና አትክልት ዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሪ ታይቷል፡፡ በተጨማሪም የሚቀዳ የምግብ ዘይት ዘይትና ቅቤ፣ ቡናና ለስለሳ መጠጦችም ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን፤ ከውጭ የሚመጣው የምግብ ዘይት ላይ መጠነኛ ቅናሽ መመዝገቡ ተገልጿል።

በሌላ በኩል፤ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የሐምሌ ወር 2014 ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር 2013 ጋር ሲነፃፀር የ30 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡

ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥም፤ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ አነቃቂዎች (ጫት)፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጅ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መስሪያ እቃዎች (የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ኪዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማሰገጫዎች)፣ ነዳጅ፣ ህክምናና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የሐምሌ ወር 2014 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ሰኔ ወር ጋር ሲነፃፀር በ3 ነጥብ 1 ከመቶ እና የምግብ የኢንደክሱ ክፍሎች በ3 ነጥብ 7 ነጥብ ከመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ወቅት የምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት በ2 ነጥብ 1 ነጥብ ከመቶ ሆኖ መመዝገቡም ታውቋል፡፡

ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት ምጣኔው በመጨረሻዎቹ ኹለት ተከታታይ ወራት መካከል ያለውን የዋጋ ለውጥ ለመለካት የሚያገለግል ሲሆን፤ ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት ምጣኔው የወቅቱን ኹኔታ የሚያሳይ በመሆኑ የአጭር ጊዜ ክስተቱን ብቻ እንደሚያመላክትም ተገልጿል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply