በሕገ-ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች እንዲመዘገቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

ኢትዮጵያ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጪ ሀገር ዜጎች ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንዲመዘገቡ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አሳሰበ።

የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ማስተዋል ገዳ÷ ምዝገባው ቪዛ እና የመኖሪያ ፈቃዳቸው አገልግሎቱ ያለፈ እንዲሁም የድርጅት ምዝገባ ሳያደርጉ ተቀጥረው የሚሠሩትን የውጭ ሀገር ዜጎች እንደሚመለከት ገልጸዋል።

ምዝገባው የሚካሄደው በአገልግሎቱ ዋና መስሪያ ቤት ሲሆን በመንግሥት የሥራ ሠዓት ሠነዶቻቸውን በመያዝ መጥተው ሕጋዊ ማድረግ አለባቸው ተብሏል፡፡

አገልግሎቱ ባደረገው ማጣራት ከ21 ሺህ የሚበልጡ የውጭ ሀገር ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚኖሩ ማወቅ ተችሏል።

ቀደም ሲል የወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከ8,000 በላይ ኤርትራውያን በአገራቸው ያለውን ሥርዓት በመቃወም ወደ ኢትዮጵያ ይሰደዳሉ።

ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ውስጥ በነበሩ አራት የስደተኛ መጠልያ ጣቢያዎች 100 ሺህ የሚሆኑ ኤርትራውያን ስደተኞች ተጠልለው የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ተበታትነው ይገኛሉ።

ሽመልባ እና ሕፃፅ የተባሉ የኤርትራ ስደተኞች መጠልያ ጣቢያዎች በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ መሆናቸውን ይነገራል። በዚህ ምክንያትም በርካቶች አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ከተሞች መበተናቸውን ይታወቃል።

በተለይ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኩል ደግሞ በስደተኞች ላይ ተገቢ ቁጥጥር ስለማይደረግ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሐሺሽን ጨምሮ ሕገወጥ ንግድ እንዲሁም በጦር መሳሪያ የተደገፈ ዝርፊያ እንደሚፈጸም በመግለጽ መንግስት አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርግ ሲወተውቱ ይደመጣል።

በኢትዮጵያ ከኤርትራውያን ስደተኞች ባሻገር በርካታ ሶማሊያውያን ስደተኞችም በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ ።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply