
በመተማ ወረዳ አኩሸራ በተባለ ቀበሌ በታጣቂዎች ከታገቱት 7 አማራዎች መካከል 2 ወዲያውኑ ሲገደሉ፣ 1 ቆስሏል፤ 4ቱ ደግሞ ታግተው ወደ ጫካ መወሰዳቸው ታውቋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ሰኔ 24/2015 ዓ/ም_ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አኩሸራ በተባለ ቀበሌ ሰኔ 24/2015 ከታገቱት 7 አማራዎች መካከል 2 ወዲያውኑ ሲገደሉ፣ 1 ቆስሏል፤ 4ቱ ደግሞ ታግተው ወደ ጫካ ስለመወሰዳቸው ታውቋል። በመተማ በአኩሸራ ቀበሌ ኩመር ከተማ ነዋሪ የሆኑት 7 አማራዎች ለቅሶ ለመድረስ ከመቸላ ቀበሌ አባይ ጊዮርጊስ በተባለ አካባቢ እንደደረሱ በታጠቁ አካላት በተኩስ የታጀበ እገታ የተፈጸመባቸው ሲሆን በጥቃቱም:_ 1) ቄስ አበጀ ሀጎስ እድሜ 45 የሆነ እና 2) ታደሰ ደርሶ የተባሉ የ60 ዓመት የእድሜ ባለ ጸጋ የሆኑት ነዋሪዎች እያንዳንዳቸው በ3 ጥይት ተመተው ተገድለዋል። አቶ አስቻለው ተጌ የተባለ ነዋሪ ደግሞ የቀኝ ትክሻውን በ1 ጥይት ተመቶ ቆስሎ በማምለጡ ወደ ገንዳውሃ ለህክምና መላኩ ተሰምቷል። በታጣቂዎቹ ታግተው ወደ ጫካ የተወሰዱትም:_ 1) ቄስ ተገን ሽበሽ፣ 2) አንዱ ዓለም አሰፋ፣ 3) አይቶ አጣናው እና 4) ተስፋሁን አባታለም የተባሉት የኩመር ነዋሪዎች ናቸው። በገበሬዎች ላይ የጭካኔ ግድያ እና እገታ የፈጸሙ አካላት እነ ማን ናቸው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የፖሊስ መረጃ ዋና ሳጅን ሲሳይ ገዳሙ ሰኔ 1/2015 በመተማ ወረዳ መቃ በተባለ ቀበሌ የሚኖሩ የቅማንት ተወላጅ የሆኑ ግለሰቦች በጫካ በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አማራዎች ተገድለውብናል በሚል በስመ አማራ የተፈጸመባቸው ጥቃት ስለመሆኑ በመግለጽ ጉዳዩን ደም ምለሳ ከሚል ጎጅ ባህል ጋር አያይዘውታል። ዋና ሳጅን ሲሳይ ገዳሙ ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ስምሪት ስለመደረጉ፣ እሳቸውም በስፍራው ተገኝተው አስከሬንና ቁስለኛ ስለማንሳታቸው ተናግረዋል። የአካባቢውን ነዋሪዎችን በመጠየቅም በእለቱ ስለተፈጸመው ግድያ እና እገታን በተመለከተ ለአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) መረጃ አጋርተዋል። የእገታ ወንጀል በየጊዜው እየተፈጸመ መሆኑን የገለጹት ዋና ሳጅኑ ብዙውን ጊዜ የአጋች ቤተሰቦችን በመያዝ ጭምር ታጋቾችን የማስለቀቅ አማራጭን እስከመጠቀም መድረሳቸውን ተናግረዋል። ይህን አሳሳቢ የሆነ ችግርን ለመፍታትም ማህበረሰቡ እርስ በርስ በመናበብ መንቀሳቀስ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል። በመተማ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች በጫካ የሚንቀሳቀሱ ጸረ አማራ አፈና፣ እገታ እና ግድያ በመፈጸም የህወሓትን ተልዕኮ እየተገበሩ የሚገኙ የቅማንት ተወላጅ የሆኑ ሽፍቶች ስለመኖራቸው በመግለጽ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረቡ ነው። እንደአብነትም በመተማ ወረዳ ሽንፋ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሽኩርያ በተባለ አካባቢ ሰኔ 6/2015 ከቀኑ 12 ሰዓት ገደማ በእርሻ ማሳቸው ላይ:_ 1) ሞገስ ፍቃዴ፣ 2) አራጌ ደርሶ እና 3) አየሁ ሽባባው የተባሉ ጀግና አራሽ እና ተኳሽ ወጣቶችን እንዲሁም፣ 4) ከሽንፋ በቅርብ ርቀት ልዩ ስሙ ማጠቢያ በተባለ አካባቢ ደግሞ ሰኔ 10/2015 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ገደማ ደግሞ ዲያቆን ጌጤ ጥላሁን የመካነ ህይወት ሽንፋ ማርያም አገልጋይ በጥይት ስለመገደላቸው የዐይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወቃል።
Source: Link to the Post