በመተከል ዞን በተደጋጋሚ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ የሚያደርጉ አመራሮችና ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ የህግ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተለያዩ ቀበሌዎች ባለው የጸጥታ ችግር የሰው ሕይወት ማለፉ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው፡፡በክልሉ ጥቃት አድራሾች ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው ቢልም ጥቃቱ ከመቆም ይልቅ እየተባበሰ በመምጣቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡ጠበቃና የህግ ባለሙያ አቶ መንግስቱ አሰፋ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሲነሱ ለነበሩ ችግሮች ህውሓት ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ መሆኑን በመግለጽ አሁን ላይ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ህወሓትን በቁጥጥር ስራ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የህወሓት ጣልቃ ገብነት አሁን የተመናመነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየጊዜው በመተከል ዞን ለሚነሳው ችግር ተጠያቂነትና ኃላፊነትም ሊወስዱ የሚገቡት የክልሉ አመራሮች ናቸው ሲሉ የህግ ባለሙያው አቶ መንገስቱ ገልጸዋል፡፡ሌላው ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ ነብዩ ምክሩ በበኩላቸው ዜጎች ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮ በሀገሪቱ መኖር እንዳለባቸው በህገ መንግስቱ ተደንግጓል፤ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን የዜጎች መብት ማስከበርና መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቋሚ ነው ይላሉ፡፡በመሆኑም በመተከል ላይ በተደጋጋሚ ችግር እንዲፈጠር ያደረጉ ግለሰቦች ከአስተዳደራዊ ቅጣት ጀምሮ በወንጀል ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ገልፀል፡፡

የፌዴራልና የክልሉ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ጥቃት ሊያስቆሙ እንደሚገባቸው የህግ ባለሙያዎቹ የገለጹ ሲሆን በአመራሮች ላይ ተገቢውን ቅጣትና እርምጃ መውሰድ ላይ ቸልተኝነት መታየት እንደሌለበትም ተጠቁሟል፡፡

********************************************************************************

ቀን 08/04/2013

Source: Link to the Post

Leave a Reply