በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የአባይ ዳር ቀበሌ ህዝብ፣ከሚሊሻውና ከህዝባዊ ከሆኑ ከልዩ ኃይል አባላት ጋር በመሆን ከተማዋን ተደግሶላት ከነበረው የኦነግ፣የጉምዝ፣የትሕነግና ሌሎች የተደራጁ ሽፍ…

በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የአባይ ዳር ቀበሌ ህዝብ፣ከሚሊሻውና ከህዝባዊ ከሆኑ ከልዩ ኃይል አባላት ጋር በመሆን ከተማዋን ተደግሶላት ከነበረው የኦነግ፣የጉምዝ፣የትሕነግና ሌሎች የተደራጁ ሽፍቶች ጥቃት መታደግ መቻሉ ተነገረ፤ አሁንም መንግስት ትልቅ ስራ ይጠብቀዋል ተብሏል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የአማራ ሚዲያ ማዕከል ከቋራ ወረዳ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ከፋለ ብርሌ ጋር ያደረገውን ቆይታ መሰረት በማድረግ የሚከተለውን ዝርዝር መረጃ ማጋራት እንወዳለን:_ አባይ ዳር ቀበሌ ከምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በእግር የ20 ደቂቃ በሚወስድ ርቀት ላይ የምትገኝና በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ስር ያለች ቀበሌ ናት። ከፍተኛ ቁጥር ያለው አማራ እና ሌሎች የሚኖሩበት ነው። በዳንጉር ወረዳ በአማራው ላይ ግድያ፣እገታ፣ያለአግባብ ጦር መሳሪያ ማስወረድ፣ሰሊጥ መዝረፍና ገንዘብ መቅጣት የተለመደ ተግባር በመሆኑ የቋራ ወረዳ እና የዳንጉር ወረዳ በጥሩ መግባባትና በመነጋገር የቀጠናውን ችግሮች ለመፍታት ብዙ ስራ ሰርተዋል። የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም 80 የሚሆኑ የኦነግ ሸኔ፣የጉምዝ ታጣቂዎችና የትሕነግ የተደራጁ ሽፍቶች ከአካባቢው የልዩ ኃይል አመራር ጋር በመስማማት ከጫካ በመምጣት በአባይ ዳር ት/ቤት ሰፍረዋል። በአካባቢው ያሉ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የልዩ ኃይል አባላትም ቀርበው ለምን እንደመጡ ጠይቀዋል። የሽብር ቡድኖችም አባይ ዳር ቀበሌ ላይ ካምፕ ለመስራትና ህዝቡን ከአካባቢው ጠራርገው ለማፈናቀልና ለመጨፍጨፍም ጭምር የመጡ መሆናቸው በመታወቁ ልዩ ኃይሎቹ ከሁለት ተከፈሉ። በውስጥ ሲገናኙ ከነበሩ የልዩ ኃይሉ አመራር መቶ አለቃ ቸኮልና ሌሎች ውስን የጉምዝ ተወላጅ አባላት ውጭ 17 የሚሆኑት አሰላለፋቸውን ከህዝብ ጋር አድርገዋል። ችግሩን በውይይት መንገድ ለመፍታት የሚቻል ከሆነ በሚል ወደ አባይ ዳር ቀበሌ ያቀኑት የቋራ ወረዳ የህዝብ ሰላም እና ደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከፋለ ብርሌ ከሌሎች 2 አመራሮችና 3 አጃቢዎቻቸው ጋር አቅንተዋል። እነ አቶ ከፋለ ህዝቡን እንዲሰበስቡ በማድረግ ከዛው ለመጨፍጨፍ እቅድ ይዘው እንደነበረ ከዛው ህዝባዊ ከሆኑ የልዩ ኃይል አባላት የተገኘው መረጃ አመልክቷል ይላሉ አቶ ከፋለ። በዚህም ውይይቱን ሰርዘዋል። ከመቶ አለቃ ቸኮል ጋር ተገናኝተው በአባይ ዳር ቀበሌ ሲንቀሳቀሱ ቀጥታ ተኩስ ተከፈተባቸው፤መቶ አለቃውም በቀጥታ አፋኙን ቡድን ለመቀላቀል እሮጠ ስለነበር ተመቷል። የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 10:30 እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ ከባድ የተኩስ ልውውጡ ቀጠለ። የቀበሌው ሚሊሾች፣17ቱ የልዩ ኃይል አባላትና ህዝቡን ይዘው እነ አቶ ከፋለ ብርሌን፣ ራሳቸውን ብሎም የአባይ ዳር ቀበሌን ከመጨፍጨፍ ታደጉ። የተደራጁ ሽፍቶችም ምንም እንኳ የቡድን መሳሪያዎችን የያዙ ቢሆኑም የበረታ የህዝቡን ትግል መቋቋም ባለመቻላቸው እግሬ አውጭኝ ብለው በዳንጉር ወረዳ አውልታ ወደተባለ ማሰልጠኛ ጫካ ፈርጥጠዋል። በነበረው የተኩስ ልውውጥም የሰዎች ህይወት አልፏል፤ የቆሰሉም አሉ። ሲቪል የለበሱት መቶ አለቃ ቸኮል ሊቀላቀሏቸው ሲሄዱ ከሽፍቶች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል። የተመቱት ከልዩ ኃይሎች የተተኮሰ ጥይት ነው የሚሉም አሉ። አባይ ዳር ቀበሌ መሃል ከተማ ላይ በቡድኑ ከተገደሉት መካከል አቶ ታደለ በለጠ እና ተካ የተባሉ አማራዎች ተገድለዋል፤ አያና የተባለ የልዩ ኃይል አባልንየሆነ በርታ እና ከ5 በላይ አማራዎች ቆስለዋል። ፀረ አማራና ፀረ ኢትዮጵያ የሆነው የሽፍቶች ስብስብ ለጊዜው እግሬ አውጭኝ ብሎ ወደ አውልታ ሲፈረጥጥ በዳንጉር አውጀኒስ በተባለ አካባቢ በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩትን የአቶ አስፋው መከተን ልጅ ሲያቆስሉ አቶ እሸቱ ጥላሁን የተባሉ አማራን የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ገድሏል። ቀጠናው ለአማራ እና ለቤንሻንጉል ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያም ወሳኝ በመሆኑ የፌደራል መንግስት እጁን አስገብቶ እንዲሰራ ነው የቋራ ወረዳ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ከፋለ ብርሌ የጠየቁት። ብልቱ እየተቆረጠ፣የደም ሴሉ እየተመዘዘ የከበሮ መምቻ እየሆነ ያለው አማራውም ሆነ የፌደራልና የቤንሻንጉል ክልል መንግስት በሰላም ጉዳይ ወሰን ሳያበጅና ሳይገድበው ገብቶ መታገል አለበት፤ በዚህ በኩል ማንም ቅር ሊለው አይገባም፤ እያለቀ ያለው ንፁሃን ነውና ያሉት አቶ ብርሌ በዳንጉር ወረዳ አቡልታ የተባለው የሽፍቶች የማሰልጠኛ ቦታ በአስቸኳይ እንዲመታ ጠይቀዋል። አሁንም ህዝቡ ዋስትና የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ መንግስት አስቸኳይና የተባበረ እርምጃ መውሰዱ ህዝቡን ከመታደግ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል። ከቋራ ወረዳ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ጽ/ቤት ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ከፋለ ብርሌ ጋር ያደረግነውን ሰፋ ያለ ቆይታ በአሚማ የዩቱብ አድራሻ ይጠብቁ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply