“በመተከል ዞን ፓዌ ወረዳ ታጣቂዎች በአማራ ላይ የሚፈፅሙትን ግድያንና ዝርፊያ የሚያስቆም አካል ማግኘት አልተቻለም፤ በወራት ልዩነት አባት እና ልጅ ተገድለዋል” ሲሉ የህዳሴ ቀበሌ ነዋሪዎች…

“በመተከል ዞን ፓዌ ወረዳ ታጣቂዎች በአማራ ላይ የሚፈፅሙትን ግድያንና ዝርፊያ የሚያስቆም አካል ማግኘት አልተቻለም፤ በወራት ልዩነት አባት እና ልጅ ተገድለዋል” ሲሉ የህዳሴ ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በተለይም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘረፋ እና ግድያው ያልተቋረጠ መሆኑን የገለፁት በመተከል ዞን የፓዌ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በአማራ ላይ ግድያና ዝርፊያ እየፈፀሙ ያሉት የጉምዝ ታጣቂዎች መሆናቸውን የጠቆሙት በፓዌ ወረዳ የህዳሴ ቀበሌ ነዋሪ የግድያ አፈጻጸሙም አስከፊ መሆኑን ተናግረዋል። እንደአብነት ሲጠቅሱም ግንቦት 1 ቀን በ2011 ዓ.ም አቶ ደጉ በየነ የተገደሉ ሲሆን በወራት ልዩነትም አቶ አብደላ የተባሉ ነዋሪም ከታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል። ቄስ ፍሬው አዩ በ2011 ዓ.ም ተገድለዋል፤ በ2012 ዓ.ም መጋቢት 10 ቀን አበበ ካሴ የሚባል ላም እረኛም በአሰቃቂ ሁኔታ በቀስትና በስለት ሲገደል ሌላኛው አንድ አማራ ከነፍሰ ገዳዮች ግድያ አምልጧል። በተመሳሳይ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም አቶ ገብሬ ደጌ ላም እየጠበቁ ሳለ “ኧረ በህግ አምላክ፣ ኧረ ድረሱልኝ እያሉ!” በጉምዝ ታጣቂዎች በጭካኔ በጥይትና በስለት ተገድለዋል።በወቅቱም ወደ 38 ቁም ከብቶች ተዘርፈዋል። በሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም 2 ንፁሀን አማራዎች ሲገደሉ አቶ ስጦታው በለጠና ማሩ ግራዝማች በሚያዚያ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ተገድለዋል፤ አቶ ቻሌ ዘሪሁን ደግሞ በከፍተኛ ቆስለው አካላቸው ቢጎድልም በህይወት ተርፈዋል። ከ7 ወራት በፊት አባቱን አቶ ገብሬ ደጌን የገደሉት የጉምዝ ታጣቂዎች ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ልጁን ወጣት ሞኝነት ገብሬን ከብቶችን እየጠበቀ ሳለ ስለመግደላቸው አሳዛኝ የጭካኔ ወንጀልም ተናግረዋል። ታጣቂዎች ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ በህዳሴ ቀበሌ አባይ በር አካባቢ አንድ ላም እረኛ ሲገድሉ፣አቶ ገበየሁ በላይ የተባሉ አባትን ክፉኛ አቁስለዋል። የክልሉ መንግስት ከሞትን በኋላ አስከሬን ከማንሳት ያለፈ ከነፍሰ ገዳዮች ሊታደገን አልቻለም ያሉት የህዳሴ ቀበሌ ነዋሪዎች ምንም እንኳ ታጣቂዎች የት እንዳሉ ቢታወቅም እርምጃ ሲወሰድባቸው አላየንም ሲሉም አክለዋል። በ2011 ዓ.ም እስከ አዲስ አበባ ድረስ ለቅሬታችን ምላሽ ይሰጠን በሚል ተወካዮችን ብንልክም እስካሁን ግን በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊት አልሰፈረም ብለዋል። መንግስት ህጻናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞችን ህይወት ከነፍሰ ገዳዮች መታደግ ካልቻለ ለስኳር ልማት በሚል ወደነጠቀን መሬታችን ሊመልሰን ይገባል ብለዋል። ለፓዌ ወረዳ የመንግስት አካላት በለስ ጫካ ተደብቀው አማራን እያደኑ የሚገድሉ ታጣቂዎችን ስም ዝርዝር ነግረናል፤ ዳሩ ግን መፍትሄ የሚሰጥ አካል አላገኘንም፤ ልጅ ማሳደግ፣ሀብት ማፍራት አልቻልንም ብለዋል። በፓዌ ወረዳ በህዳሴ ቀበሌ ብቻ እስካሁን ከ600 በላይ ከብቶች ተዘርፈዋል ሲሉ ነው ነዋሪዎች የተናገሩት። በመተከል ዞን የፓዌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ አሰፋ ንፁሀን አማራዎች በታጣቂዎች እየተገደሉ መሆናቸውን አምነው ችግሩን ለመፍታትም በህዳሴ ቀበሌ እንዲሰፍሩ እየጠየቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ጫካ በመሆኑ ለማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ እንጅ ታጣቂዎቹ እንደሚታወቁ የገለፁት አቶ ብርሀኑ ተገቢ የሆነ እርምጃ እንዲወስድ ኮማንድ ፖስቱን እየጠየቅን ነው፤ ከዛም በላይ ግን ሰው ተደራጅቶ ራሱን እንዲጠብቅም እየሰራን ነው ሲሉም አክለዋል። በፓዌ ወረዳ ከህዳሴ ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር የተደረገውን ቆይታ በአሚማ የዩቱብ አድራሻ ይጠብቁ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply