በመንግስታቱ ድርጅት የተቋቋመው የመርማሪ ቡድን የሥራ ጊዜ ሳይራዘም ቀረ

– የአውሮፓ ህብረት፣ የመርማሪ ቡድኑ የሥራ ጊዜ እንዲራዘም የሚያስችል  ረቂቅ ሃሳብ አለማቅረቡ ተኮንኗል
 በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር   በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን  የተቋቋመው የባለሞያዎች ቡድን የምርመራ ጊዜ እንዲያራዝም  በበርካታ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች  በተደጋጋሚ ጥሪ ሲደረግ ቢቆይም፣ የመርማሪ ቡድኑ የስራ ጊዜ ሳይራዘም ቀርቷል።
የመርማሪ ቡድኑ የስራ ጊዜ ሳይራዘም የቀረው ከየትኛውም የአለም ክፍል ለመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ቡድኑ የቆይታ ጊዜውን  እንዲያራዝም የሚጠይቅ  ረቂቅ ሀሳብ ባለመቅረቡ  መሆኑ ታውቋል።
የዓለማቀፉ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን የጊዜ ቆይታን ለማራዘም ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የማቅረቢያው ቀነ ገደብ ከትናንት በስቲያ ተጠናቋል።  ለኮሚሽኑ መቋቋም ቁልፍ ሚና የተጫወተው አውሮፓ ኅብረት፣ የኮሚሽኑን ቆይታ ለማራዘም የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም ሣያቀርብ ቀርቷል ።  
የሂዩማን ራይትስ ዎች የአውሮፓ ዳይሬክተር ፊሊፕ ደም፣ የአውሮፓ ህብረት፣  የመርማሪ ቡድኑ የስራ ጊዜ እንዲራዘም ረቂቅ ሃሳብ አለማቅረቡን አጥብቀው ኮንነዋል፡፡
የመርማሪ ቡድኑ እንዲቋቋም የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ ያጸደቀው አውሮፓ ኅብረት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ሂዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡለት  ቆይተዋል ።   ሂዩማን ራይትስ ዎች፣  የአውሮፓ ህብረት  የቡድኑ የምርመራ ጊዜን እንዲያራዝም  በማድረጉ ረገድ  ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅበትም አመልክቷል ።
ተበዳዮችም ሆኑ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች፣ የሀገሪቱ  የፍትህ ተቋማት ፍትህ ያሰፍናሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚገልፀው  አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም፤  አለም አቀፉ የመርማሪዎች ቡድን እንዲቋቋም ከፍተኛ ሚና የተጫወተው የአውሮፓ ህብረት አሁንም የስራ ግዜው እንዲራዘም ረቂቅ ሃሳብ በማዘጋጀት ረገድ የመሪነት ሚና እንዲጫወት ሲወተውት ሰንብቷል።  
በዓለማችን ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ታላላቅ የሰብአዊ መብት  ጥሰቶች ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ በመሆን የመንግስታቱ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት  እንዲመረምር  ያቋቋመው ቡድን ተልዕኮውን ለተጨማሪ አንድ አመት እንዲያራዝም  መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን ጥያቄውን ያቀረቡት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ኦክ፤ስፋም እና የአለም የሰላም ፋውንዴሽንን ጨምሮ 63 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ በጻፉት ደብዳቤ ነበር ።
የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ (ICHREE) ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት በኢትዮጵያ አሁንም የጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደቀጠሉ መሆናቸውን አመልክቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply