በመንግስት እና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ተኩስ ማስቆም ዋና ዓላማችን ነው- ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) “ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ” በሚል ስያሜ አገር አግቀፍ የዕርቅ እና ሰላም ሂደት መጀመሩን ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፋቸውን ሰጥተውታል። 

15 የሚደርሱ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮችና ተወካዮች በተገኙበት ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ስብሰባ የተደረገ ሲሆን ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች የተካተቱበት ጊዜያዊ ኮሚቴ መቋቋሙን የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መሐመድ አወል ሀጎስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ነእፓ በአገሪቷ ውስጥ እየተካሄዱ የሚገኙ የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭቶችን ለማስቆም “ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ” በሚል ስያሜ ያዘጋጀውን የእርቅና የሰላም ሃሳብ መጋቢት 9 ቀን 2016 ይፋ ማድረጉን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም። 

በፓርቲው ጽህፈት ቤት በተካሄደው ስብሰባ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየተካሄዱ ያሉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸው ግጭቶቹ በዚህ ከቀጠሉ የአገር ህልውናን ሊያጠፋ የሚችል አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አሳስበዋል። በየአካባቢው የሚካሄዱ ግጭቶችም በተቻለ ፍጥነት ሊቆሙ ይገባል በማለት የእርቅና ሰላም ሃሳቡን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

ለሁለት ዓመታት በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች የተካሄደው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መቅጠፉ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን፤ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ዛሬም ድረስ የቀጠሉ ጦርነቶች የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፉ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል። 

የውይይቱ ተሳታፊዎች አሁን ላይ ያሉ ግጭቶች እልባት ካላገኙ በየአካባቢው ሌሎች አዳዲስ ግጭቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ጠቋሚ ምልክቶች እየታዩ እንደሆነ መግለጻቸውንም የነእፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በተለይ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። 

በሀገረ መንግስት ግንባታ ዙሪያ የተለያየ ትርክት መኖር፣ በአብዛኛው ነውጥ የተጫነው የፖለቲካ እና የመንግስት ታሪክ፣ የአገሪቷ ነባር ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ውቅር ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈጣን እና ተለዋዋጭ ብሂሎች ጋር አለመጣጣም፣ ለረጅም ዘመናት ቅቡልነት ያላቸው መንግስታት አለመኖር፣ ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍትህ ለማስፈን የአገር መሪዎች የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማጣት ለግጭቶቹ ምክንያት መሆናቸውም ተመላክቷል።

እንደ ሕዝብ ግንኙነቱ ኃላፊ ገለጻ፤ ትላንት አምስተኛ የምስረታ ዓመቱን ያከበረው የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ “ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ” በማለት ያቀረበውን የእርቅ እና የሰላም ሐሳብ ሙሉ ድጋፋቸውን በመስጠት እገዛ እንደሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል። 

በዚህ የእርቅ ሂደት ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው ከተለዩ ተግዳሮቶች መካከል ታጣቂ ኃይሎችን እና መንግስትን ለማቀራረብ የሚደረገው ሂደት ከባድ መሆን አንዱ ነው። እንዱሁም በመካከላቸው የተራራርቁ እና “ሊታረቁ የማይችሉ” አጀንዳዎች መኖር፣ ሁሉንም የሚያስማማ አሸማጋዮችን መለየት እና የበጀት እጥረትም ሊያጋጥሙ ሂደቱን ሊፈትኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።  

“መፍትሄው አንድ ነው፤ ሰላምና እርቅ” የሚሉት የነእፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ችግሮቻችን ፖለቲካዊ በመሆናቸው መፍትሔዎቻችንም ፖለቲካዊ ናቸው ብለዋል። የእርቁ አላማ ነፍጥ አንግበው የሚዋጉ ኃይሎች እና መንግስት መካከል እርቅ በማውረድ ጊዜ የማይሰጠውን ጉዳይ የጦር መሳሪያዎችን ተኩስ ማስቆም መሆኑን በአጽንዖት ገልጸዋል።  

“ዋናው አላማ የተኩስ አቁሙ ከተሳካ”፤ ከዛ በኋላ የሚኖረውን ሂደት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎችም አካላት የሚሰሩት የቤት ስራ መሆኑን ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አስታውቋል።  

የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው “እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር በአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ብቻ የሚፈታ ባይሆንም፤ ነገር ግን እንደድርሻችን ለሰላምና ለእርቅ ጠጠርም ብትሆን መወርወር አለብን” በማለት ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቀናት በፊት “ከታማኝ” ግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ከሰላም ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው። በሽፍትነትና አመጽ በሚመስል ነገር ከእንግዲህ በኋላ የኢትዮጵያን መንግስት መጣል ሳይሆን መነቅነቅ አይቻልም” ማለታቸው አይዘነጋም።

በቀጣይ በርከት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት መድረክ ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ መደረሱንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች። 

ነእፓ የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ “በጉዟችን መጀመሪያ በታላቅ ደስታ እና ተስፋ የተቀበልነው የለውጥ ሂደት መላ የሀገራችን ህዝቦች ከጠበቁት እና ተስፋ ካደረጉበት አቅጣጫ ወጥቶ የለውጡ ትሩፋቶች በጠወለጉበት፣ የፖለቲካ ምህዳሩ በተሸበሸበበት፣ መልካም አስተዳደር በታመመበት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራር በተንሰራፋበት፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት በጠፉበት የታሪክ አጋጣሚ ነው” ሲል ገልጿል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply