በመንግስት የአመራር ቦታ ላይ የተቀመጡ የስራ ኃላፊዎች መረጃን ለመገናኛ ብዙሃን የመስጠት ፍላጎት ማጣት ለሀሰተኛ መረጃ መበራከት ምክንያት መሆኑን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል፡፡

ችግሩን ከማቅለል ይልቅ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የሀሰት ትርክቶችንና መረጃዎችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተለያዩ የብሮድካስት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በመልቀቅ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው ብሏል፡፡በዚህም በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ስራን የተለያዩ አካላት በቡድንና በተናጠል መፈፀማቸው በየጊዜው ተስተውሏል ብሏል ተቋሙ፡፡

ትክክለኛ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ወይም ጋዜጠኞች ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆኑ የመንግስት ኃላፊዎች በሀሰተኛ መረጃዎች ለሚደርሱ ውዥንብሮች ዋነኛ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ይህንን ያሉት በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነፃነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማናየ አለሙ ናቸው፡፡

የመንግስት ተቋማት አመራሮች በህግ ከተለዩ ሚስጥራዊ መረጃዎች ውጪ ማንኛውንም መረጃ ለጋዜጠኞች እና መረጃን ለሚፈልግ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የመስጠት ግዴት እንዳለባቸውም አስታውሰዋል፡፡የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር የመንግስት ኃላፊዎች እና የተቋማቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን ሊያውቁት ይገባልም ብለዋል፡፡

የመረጃ ነፃነት አዋጁን የማሻሻል ስራ በባለሙያዎች እየተከወነ ነው ያሉት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነፃነት ዳይሬክተሩ፤ መረጃን የሚከለክሉ የመንግስት ኃላፊዎች ሊወሰድባቸው የሚገባ እርምጃ በአዋጁ ይካተታል ብለዋል፡፡

ቀን 22/06/2013

አሐዱ ራዲዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply