በመከላከያ ሰራዊት ላይ ህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን የፈፀመው ጥቃት ከባዕድ ወረራ የከፋ የከሃዲነት እርምጃ ነው-ም/ጠ ሚኒስትር አቶ ደመቀ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመከላከያ ሰራዊት ላይ ህወሃት ውስጥ ያለው ቡድን የፈፀመው ጥቃት ከባዕድ ወረራ የከፋ የከሃዲነት እርምጃ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ሴክሬታሪያት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መግለጫ ሰጥተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የክብር እና የሉዓላዊነት መለያ በመሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈፀመው ጥቃት ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የሚፈልገው ቡድን የመጨረሻ የክህደቱ ተግባሩ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ ልዩ ሀይልን በማንቀሳቀስ በአማራ ህዝብ ላይ ወረራ ለማካሄድ ከፍተኛ ርብርብ ማካሄዱንም አስታውቋል።

ለትግራይ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ከሃዲ ቡድኑ ህዝብን መሸሸጊያ በማድረግ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተለያዩ ሴራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፤ አሁንም ወደ ከፋው ጫፍ እየተራመደ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያ ማህፀን የሆነው የትግራይ ህዝብ በዚህ ወቅት ታሪክ ሰሪነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ሴክሬታሪያቱ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው ÷ አሁን የተፈጠረው ግጭት በትግራይ መንግስት እና በፌዴራል መንግስት መካከል የተከናወነ እንዳልሆነ አንስተዋል።

ግጭቱ ከመላው የህወሃት መዋቅር ጋር የተፈፀመም አይደለም÷ ይልቁንም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚፈልግ ህወሃት ውስጥ ከተሸሸገ ቡድን ጋር ነው ብለዋል።

በአላዛር ታደለ

The post በመከላከያ ሰራዊት ላይ ህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን የፈፀመው ጥቃት ከባዕድ ወረራ የከፋ የከሃዲነት እርምጃ ነው-ም/ጠ ሚኒስትር አቶ ደመቀ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply