በመዲናዋ ለ1 ወር በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተነገረ

ዕረቡ ሐምሌ 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ከግሪንቴክ ኢትዮጵያ ጋር በመሆን በቀጣዩ አንድ ወር በኤሌትሪክ በሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱን አስታወቀ።

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር በዛሬዉ ዕለት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ የማስተዋወቂያ መድረክ ያከናወነ ሲሆን፤ መድረኩም በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ገበያዉ ለማስገባት ከሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ አንዱ እርምጃ መሆኑ ተነግሯል።

በመድረኩም የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ እንደተናገሩት፤ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት በኢትዮጵያ 4 ሺህ 800 የኤሌክትሪክ አዉቶብሶችን እንዲሁም 148 ሺህ የኤሌክትሪክ አዉቶሞቢሎችን ለማስገባት ታቅዷል።

ኢትዮጵያ ለነዳጅ በዓመት የምታወጣዉን 4 ቢሊዮን ዶላር ወጪን ለማዳን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸዉም አብራርተዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ከመገንባት አንጻር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸዉ የግሪን ቴክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲትራ አሊ ተናግረዋል።

በቀጣይም ተቋሙ አዉቶሞቢሎች፣ ሚኒባስ እና ሚዲባሶች፣ አምቡላንሶች፣ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች የተሽከርካሪዎች አይነቶችን ለማምረትም እቅድ እንዳላቸዉ አስታዉቀዋል።

በቀጣይም አንድ ወር የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስተዋወቅ 60 በሆኑ ተሽከርካሪዎች በአዲስአበባ ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽት 1 ሰዓት እሁድ እና የበዓል ቀናትን ጨምሮ ነጻ የትራንስፖርት አግልግሎት እንደሚሰጡም መገለፁን ብስራት ራዲዮ ዘግቧል።

ለዚህም በአዲስአበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የተተከሉ 40 የሚሆኑ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply