በመዲናዋ የስነጥበብና የሳይንስ ሙዚየም በዛሬው ዕለት ተመረቀ

የፓን አፍሪካ ኢንተለጀንስ ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ነው

ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በመዲናዋ አዲስ አበባ አስደናቂ የቀለበት ቅርጽ ያለው ህንጻ እና ማራኪ የጉልላት ቅርጽ ያለው ተደርጎ የተገነባው ማዕከል እንዲሁም በአይነቱ አዲስ የሆነው የስነጥበብና የሳይንስ ሙዚየም በዛሬው ዕለት ተመርቋል።

የሳይንስ ሙዚየሙን  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  በይፋ መርቀው የከፈቱ ሲሆን፤ ለሚቀጥሉት ተከታታይ ሳምንታት ለእይታ እና ለህዝብ ክፍት የሚሆነውን የቴክኖሎጂ ጀማሪዎች እና የመንግስት/የግል ተቋማት አውደ ርዕይም አስጀምረዋል።

ሙዚየሙ በ7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በኪነ-ህንጻ ንድፍ ውስጥ ያካተተው ክብ ቅርጽም በማያቋርጥ እድገት ውስጥ ያለን እድገትና የሰው ልጆችን ጥበብ የሚያመለክት ነው ተብሏል።

በተጓዳኝም ኢትዮጵያ በአስገራሚ ፍጥነት በማደግ ላይ ካለው ቴክኖሎጂ ጋር ለመጣመር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይም እንደሆነም ተነግሯል።

የስነ ጥበብና የሳይንስ ሙዚየሙን አስደናቂ የሚያደርገው ምንድነው?

👉 ኹለት ግዙፍ ህንጻዎችን በተንጣለለ ሥፍራ ላይ ቢያሳርፍም 80 በመቶ የሚሆነው ክፍሉ ከ4 ሺሕ በላይ በሆኑ አገር በቀል ዛፎች፣ እጽዋትና ባሸበረቁ አበቦች የተሸፈነ ሥፍራ በመሆኑ አረንጓዴነቱ ጎልቶ ይታያል።

👉 ሙዚየሙ በጥንቃቄ የተዘጋጁ የመኪና ማቆሚያዎች በተጨማሪ በዙሪያው ካሉ የከተማችን ፓርኮች ጋር የሚያገናኘው ውብ የእግረኛ መንገዶች ያሉት ነው።

👉 የአትክልት ሥፍራዎቹ ጎብኚዎች አረፍ ብለው ንፋስ የሚቀበሉባቸው ምቹ መቀመጫዎችን እንዲሁም በጥበብ ሥራዎች የሚዝናኑባቸውን የስነ ጥበብና የመዝናኛ ቦታዎችን የያዙ ናቸው።

👉 ትልቁ ህንጻ ከ15 ሺሕ ሜትር ካሬ በሚበልጥ መሬት ላይ ያረፍ ሲሆን፤ አጠቃላይ ሥፋቱ 132 ሜትር ያህል ነው።

👉 ከተፈጥሮ ስርዓት ጋር ተስማሚ በሆነ መንገድ ሃይል ከሚያመነጩ የውሃ ግድቦቻችን እንዲሁም በጣሪያው ላይ ከተገጠሙ የጸሀይ ብርሃን ሰብሳቢ መሣሪያዎች የሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚያገኘው ይህ ሙዚየም ተፈጥሮአዊ የሃይል ማስተላለፊያዎችንና ሃይል ቆጣቢ የተፈጥሮ ብርሃንን የሚጠቀም ነው።

ይህ የስነጥበብና የሳይንስ ሙዚየም ትላንታችንን፣ ዛሬያችንን እና ነገአችንን በአንድ ላይ አሰናስኖ ሳይንስን ጥበባዊ በሆነ መንገድ፤ ጥበብን ደግሞ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያስቃኝ በመሆኑ አስደማሚ ተሞክሮዎችና አዳዲስ እውቀቶች የሚቀሰሙበት እንደሚሆንም ኢብኮ ዘግቧል።በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን የፓን አፍሪካ ኢንተለጀንስ ኮንፈረንስን በንግግር ከፍተዋል።

በንግግራቸውም አሁን ላይ ሳይንስ የየዕለት እንቅስቃሴ መሠረት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ አዘጋጅታ በመተግበር በአብዮት ውስጥ መሆኗን ተናግረዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቴክኖሎጂውን በግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት እና መንግስት አስተዳደር ዘርፎች በመጠቀም እመርታ እያስመዘገበ መሆኑን ገልፀዋል።

ለኹለት ቀናት የሚቆየው ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ ሲሆን፥ ዛሬ ተመርቆ በተከፈተው የሳይንስ ሙዚየም ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

ኮንፈረንሱ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አፍሪካን ማብቃት በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።

The post በመዲናዋ የስነጥበብና የሳይንስ ሙዚየም በዛሬው ዕለት ተመረቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply