በመዲናዋ የተበላሸ የቂቤ ምርት ይዞ የተገኘ ተቋም ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

ማክሰኞ ጷግሜ 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ የተበላሸ የቂቤ ምርት ይዞ የተገኘ ተቋም ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ የመድኃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ካለፈው አርብ ጀምሮ ለዘመን መለወጫ በዓል ከወረዳ እስከ ማዕከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን 811 የሚሆኑ ተቋማት ላይ የቁጥጥር ሥራ ማከናወኑ ገልጿል።

በዚህም ባለስልጣኑ ባደረገው የቁጥጥር ሥራ ለበርካታ ተቋማት የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ 1 ድርጅች ደግሞ እንዲታሸግ መደረጉ ተገልፆል፡፡ የታሸገው ተቋም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 አመዴ አካባቢ የቂቤ መሸጫ ሱቅ ሲሆን፤ የጤና ብቃት ማረጋገጫ፣ የንግድ ፍቃድ ሳይኖረው እንዲሁም ምንጩ ምን እንደሆነ የማይታወቅ 24 ማዳበሪያ ምርት በተሽከርካሪ ይዞ እና ሲሸጥ በመያዙ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም 107 ኪሎ ግራም የሚሆኑ ቂቤ፣ ስጋ፣ የባልትና የተበላሹ የምግብ ምርቶች መወገዳቸውን የባለስልጣኑ የምግብና ጤና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምሬሳ ሚደቅሳ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

የበዓል ወቅት በመሆኑ ህብረተሰቡ አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮችን በሚመለከትበት ጊዜ በነፃ የስልክ መስመር 8064 ላይ በመደወል ለባለስልጣኑ ማሳወቅ አለበት ሲሉም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply