በመዲናዋ ያለው የትራንስፖርት ችግር ዋነኛው መንስዔ የከተማው ንድፍ [ፕላን] መሆኑ ተገለጸ

በአዲስ አበባ የሚስተዋለው የትራንስፖርት ችግር ዋነኛ የትራንስፖርት ችግር መንስዔ የከተማው ንድፍ [ፕላን] እራሱ ነው ሲሉ የከተማ ትራንስፖርት ባለሞያዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። 

እንደምክንያት ያነሱትም፤ አንድ ሰው የሚኖርበት ቦታ፣ የሚሰራበት፣ ልጆቹን የሚያስተምርበት እንዲሁም የገበያ ማዕከሎች እጅግ የተራራቁ መሆናቸው ነው ይላሉ። እነዚህ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ለማድረግ የሚኖሩ የትራንስፖርት አማራጮች በወቅታዊ የኢኮኖሚ አቅም፣ ጾታ እንዲሁም ከደህንነንት አንጻር እንደሚወሰኑ ባለሞያዎች አመላክተዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ ባለሞያ “ለዚህም ነው የከተማ ፕላን ችግር አምጥቷል የሚባለው። የሰዎች መኖሪያ ቤት እና እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው ስፍራዎች መራራቃቸው። ይኸ ደግሞ የሞተር ትራንስፖርት እንድንጠቀም ያስገድደናል” ሲሉ ከዋነኞቹ ችግሮች አንዱን አብራርተዋል። 

በአዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የመፍትሔ ሃሳቦችን ሲያቀርቡ ይስተዋላል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ባይሳካም የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ ከአዲስ ዋልታ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ የትራንስፖርት አማራጮች የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ያገናዘቡ እንደሚሆኑ ጠቅላላ ሃሳብ አንስተዋል። 

በዚህም የበካይ ጋዞችን ልቀትን ለመቀነስ አሮጌ መኪና እንዲሁም በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉን ገለጸው፤ በአንጻሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። ለአብነትም አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ 60 የኤሌክትሪክ መኪና የቻርጅ ጣቢያዎች መኖራቸውን ተገልጿል። 

የሞተር ትራንስፖርት መጠቀም ካስፈለገ ደግሞ ሁሉም ሰው መኪና ሊኖረው ይገባል ያሉት ባለሙያው ከኢኮኖሚያችን አኳያ አቅም ቢኖረን እንኳን ያለው መሰረተ ልማት ሁሉንም ሰው ማስተናገድ እንደማይችል ግን ይገልጻሉ።

እንደባለሞያዎቹ ገለጻ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻራዊ መፍትሔው የሕዝብ ትራንስፖርት አማራጮችን ማስፋት ነው። ይኼውም ጊዜ መቆጠብ የሚያስችሉ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ እና የሰዎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ማደረግ ላይ ትኩረት እንደሚያስፈልግም ባለሞያዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ማስፋት ላይ መሆኑን አጽንዖት የሰጡት አንድ ባለሞያ፤ በከተማ አውቶብስ አሊያም በባቡር መልክ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ለትራንስፖርት ችግሩ እንደ መፍትሔ በቅርቡ አንድ ሃሳብ ያቀረበው ኦቪድ ግሩፕ የተባለ ኩባንያ ‘ኬብል ካር’ ወይንም በገመድ ላይ ተንጠልጣይ የሕዝብ ትራንስፖርትን ማንሳቱ አይዘነጋም።  አዲስ ማለዳ ለባለሞያዎች ይህ አዲስ አበባ ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይችላል ወይ ስትል ላቀረበችው ጥያቄ “ከመረጃው ጋር ይፋ የተደረገ ጥናት ባለመኖሩ ብዙ መናገር አይቻልም” ብለዋል።  

ነገር ግን  የአዋጭነት ጥናት ወይም የንድፍ ሰነድ ቢኖረው ማለትም፤ ክፍያው፣ አንድ ‘ኬብል ካር’ ምን ያህል ሰው ይይዛል፣ በምን ያህል ሰዓት ልዩነት ይመጣል የሚሉ ጥያቄዎች ከተመለሱ ተግባራዊ መሆን ይችላል ወይም አይችልም የሚለውን መመለስ ይቻላል ተብሏል። 

ባለሞያዎች አሁን አለ በሚሉት የከተማ ፕላን ክፍተት ባለበት የሆነው ሆኖ ይላሉ ባለሙያው “የከተማው የትራንስፖርት አውታሩ በደንብ ቢሰፋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን የመስመር አመዳደብ፣ ብዛት እንዲሁም የማመለሻ መርሐግብር በተገቢው መንገድ ቢከወን የከተማው ፕላን የፈጠራቸውን ክፍተቶች መሙላት ይቻላል” ሲሉ ገልጸዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በእግር መጓዝ፣ በእንስሳት የሚሳቡ ጋሪዎችን ማዘመንን ጨምሮ እንደ ሳይክል ያሉ ሞተር አልባ ትራንስፖርት መጠቀም እንደ አማራጭ ያቀረበ ሲሆን የተለያዩ የእግረኛ መሰረተ ልማቶች መገንባት እንደሚያስፈግም ገልጸዋል።

ይኹን እንጂ በአዲስ አበባ ከተማ ለከተማ ውበት እንዲሁም ገጽታ በሚል ባለሶስት እግር የ’ባጃጅ’ ተሽከርካሪዎች በዋና መንገዶች ላይ እንዳይጓጓዙ መከልከሉ ይታወቃል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ሰዓት አራት አዳዲስ የመንገድ ኮሪደር ግንባታ እያከናወነች ሲሆን ከመገናኛ በአራት ኪሎ ፒያሳ አድዋ መታሰቢያ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከወሎ ሰፈር በለገሃር ፒያሳ አድዋ መታሰቢያ እንዲሁም ከቦሌ እስከ መገናኛ የሚሄዱ መንገዶች ግንባታ ተጀመሯል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply