በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለህዳሴ ግድብ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

በፅህፈት ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም እንደተናገሩት፥ ዜጎች ለግድቡ የሚያደርጉት ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በተለይም ከውሃ ሙሌቱ ጋር ተያይዞ የህዝቡ ተነሳሽነትና ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ነው ያሉት።

በዚህም በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም ብቻ 109 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡

እንዲሁም ነሐሴ ወር ላይ ከ152 ሚሊየን በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን መስከረም ወር 2013 ዓ.ም ደግሞ ከ197 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በመስከረም 2013 ዓ.ም የተገኘው ገቢ እስከዛሬ ለግድቡ ግንባታ በወር ከተሰበሰበው ከፍተኛው መሆኑንም ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በመጀመሪያው በሩብ ዓመት 507 ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉንም ጠቁመዋል።

ይህም ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የህዝቦች ህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን በተግባር ያሳዩበት መሆኑን አውስተዋል።

ለግድቡ ግንባታ በአጠቃላይ 160 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት።

እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ ለግድቡ ግንባታ 121 ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፥ ከዚህ በኋላ ለሚኖረው ስራም 40 ቢሊየን ብር አካባቢ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ህዝቡም ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ያሳየውን ድጋፍና ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

The post በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለህዳሴ ግድብ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply