በማክሰኝት ከተማ ስድስት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተሰማ

ከጎንደር ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ማክሰኝት ከተማ፤ ረቡዕ ሐምሌ 12/2015 ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሦስት ፖሊስና ሦስት ሚሊሻ በድምሩ ስድስት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም አንድ ነዋሪ መገደላቸውን አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎች ሰምታለች።

የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፤ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የጸጥታ አካላት፣ የፋኖ አባላትና ነዋሪዎች ቆስለው ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።

ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 10/2015 በማክሰኝት ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የአንድ የፋኖ አመራር ታሰሮ የተለቀቀ ቢሆንም፤ የጦር መሳሪያው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መነጠቁን ተከተሎ “የፋኖውን የጦር መሳሪያ መልሱ” በሚል ከከተማዋ በቅርብ እርቀት ረቡዕ ዕለት ሌሊቱን ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ ማደሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በዚህም በማክሰኝት ከተማ የሚገኙ ኹሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ ሱቆች፣ ሆቴሎች እና ባንኮች ዝግ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።

በአካባቢው ከሐምሌ 10/2015 ጀምሮ በመንግሥት የጸጥታ አካላትና በፋኖ መካከል ነግሶ በነበረው ውጥረት ረቡዕ ማታ ከተደረገው የተኩስ ልውውጥ በኋላ መቆሙንም ነዋሪዎቹ አክለዋል፡፡

በተጨማሪም በትናንትናው ዕለት ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ በጎንደር ከተማ ከዞኑ አስተዳደር እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢሮ አጠገብ አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ባለታወቁ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት መገደላቸው ተሰምቷል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ለማግኘት ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ሙሉጌታ ምህረት የደወለች ሲሆን፤ “ስብሰባ ላይ ነኝ ትንሽ ቆይታቸሁ ደወሉ” ካሉ በኋላ፣ በተደጋጋሚ ቢደወልላቸውም ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply