በማይካድራ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል በሚል በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተገለጸው የሟቾች ቁጥር ስህተት እንዳለበት ተገለጸ።

የህወሃት ቡድን በልዩ ሃይሉ አማካኝነት በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በሰሜን ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ 18ኛ ቀኑ ላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በማይካድራ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ ቦታው ላይ በነበረው የመንግስት አስተዳድር ወይም በትግራይ የጸጥታ ሃይል አጋዥነት እና ሳምሪ በተሰኘ የወጣቶች ቡድን መፈጸሙንም በያዝነው ሳምንት ማሳወቁ አይዘነጋም።

ኮሚሽኑ በዚህ አሰቃቂ እና ማንነትን መሰረት ባደረገ የግድያ ወንጀል በማይካድራ 600 ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን ገልጿል።

የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል የገለጸው ኮሚሽኑ ክስተቱ የጦር ወንጀል የመሆን እድሉ የሰፋ ሊሆን እንደሚችልም በቅድመ ምርመራ ሪፖርቱ ጠቁሟል።

ይሁንና በቦታው ያሉ የህክምና ባለሙያዎች በኮሚሽኑ የተጠቀሰው ቁጥር ስህተት አለበት ሲሉ የህክምና ባለሙያውን ቡድን የመሩት ዶክተር ስምኦን ደሳለኝ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ስምዖን አስተያየት ከሆነ በአካባቢው በተፈጠረው ጦርነት የተጎዱ ሰዎችን ለማከም ወደ አካባቢው ማምራታቸውን ተናግረው በማይካድራ ሆን ተብሎ ግድያ የተፈጸመባቸው ሰዎች ከ750 በላይ እንደሆነ በአይናቸው ማየታቸውን እና ይሄንን አሃዝም የሰብአዊ መበት ኮሚሽን ላሰማራቸው መርማሪዎች መናገራቸውን ነግረውናል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው ጉዳዩን ለመመርመር ወደ ሰፍራው ያቀናው የምርመራ ቡድን መረጃዎችን ሐኪሞችን ጨምሮ በአካባቢው ካሉ የተለያዩ አካላትን ጠይቀው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በምርመራው የተገኘውን መረጃ ከተለያዩ ቦታዎች ስለምንቀበል በራሳችን መመዘኛ አጣርተን ነው ይፋ የምናደርገው ሆኖም ግን በዚህ አሰቃቂ ግድያ ህይወታቸው ያለፉ ዜጎች ቁጥር 600 ብቻ ነው ብለን አልገለጽንም በቀጣት ተጨማሪ እናዋናው ሪፖርት ሲሰራ ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ይታወቃል ሲሉም ዶክተር ዳንኤል ምላሽ ሰጥተውናል።

በመቅደላዊት ደረጀ
ሕዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply