በምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ዕጦት ምክንያት የሰብል መዝሪያ ወቅት እንዳለፈባቸው አርሶ አደሮቹ ተናገሩ። የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ግንቦት 15/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ወይንማ ወርቅማ ቀበሌ የሚገኙ አርሶ አደሮች ዘር እና ማዳበሪያ ተደራሽ ባለመሆኑ ሰብል መዝራት እንዳልቻሉ እና በከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ተናግረዋል። አርሶ አደሮቹ እንደገለፁት ለቀበሌው ነዋሪ ለሆኑ አርሶ አደሮች ይከፋፈላል የተባለው ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮች በገንዘብ እየተደራደሩ በህገወጥ መንገድ አንድ ቀረጢት ማዳበሪያ እስከ አስር ሽህ ብር እና አንድ ቀረጢት ምርጥ ዘር እስከ አራት ሽህ ብር እየሸጡት ይገኛሉ ብለዋል። በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠናል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪ አርሶ አደሮች ለአሻራ ሚድያ በስልክ ተናግረዋል። አርሶ አደሮቹ “በዘመናችን አይተነው የማናውቀው ነገር አጋጥሞናል፤ የሚሰማን አካል ልናገኝ አልቻልንም፤ ይህ እየሆነ ያለው ሆን ተብሎ አርሶ አደሩን በኢኮኖሚ ለማዳከም ነው” ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል። በእጅ አዙር የአማራን ህዝብ በኢኮኖሚ ለማዳከም እየተሰራ ያለው ሴራ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ብለዋል ሲል አሻራ ሚዲያ ዘግቧል። በተመሳሳይ የይልማና ዴንሳ_አዴት አርሶ አደሮችም ተመሳሳይ ቅሬታ እያቀረቡ ነው። የመንግስት አካላት በአርሶ አደሩ ላይ እየነገዱ ነው፤በዘርፉ ያሉ አመራሮች ማዳበሪያውን ለነጋዴዎች በመሸጥ አርሶ አደሩ እንዳያገኝ እየሰሩ ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል። በአመራሩ በኩል የአቅርቦት ችግር አለብን በሚል ግንቦት 15/2015 በሁለት ቀበሌ ለሚገኙ ከ1 ሽህ 700 ለማይበልጡ አርሶ አደሮች አምሳ ኪሎ ለአራት በማካፈል 12.5 ኪ/ግራም ማዳበሪያ ብቻ እንደሰጧቸው ተናግረዋል፤ “ይህችን ማዳበሪያ ምን እናድርጋት?” ሲሉም ጠይቀዋል። አርሶ አደሩ ካላመረተ ህዝብ እንዴት ይኖራል? ብለው የጠየቁት ገበሬዎቹ በተደጋጋሚ እያቀረቡት ላለው ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
Source: Link to the Post