
በምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ እውቅና ተሰጥቶት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጸው አባይ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ (አህብፓ) የክልሉ መንግስት በአመራሮቹ እና አባላቱ ላይ እየፈጸመ ያለውን እስር፣ ወከባ እና ማሳደድ እንዲያቆም ጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ አባይ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ጊዜያዊ እውቅና ተሰጥቶት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ፓርቲውን የማስተዋወቅ፣ አባላት የመመልመል፣ የማደራጀት እና የማንቃት ስራው ከጅምሩ በክልሉ መንግስት ፈተና ላይ መውደቁ ተገልጧል። ፓርቲው ከጎሳና ብሄር ውጭ የሆነ ህብረ ብሄራዊ የሆነ ክልሉ ላይ የሚገኙ ከ12 በላይ ብሄሮችን ያካተተ ፓርቲ ሲሆን የክልሉ ህገ መንግስት እንዲሻሻል የሚታገል ስለመሆኑ ተመላክቷል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት የልዩነት እና አግላይ አንቀጾችን የያዘ ህገ መንግስት መሆኑን መነሻ በማድረግ እንዲሻሻል እየሰራ መሆኑን ፓርቲው ገልጧል። ፓርቲው እንደገለጸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 12 ብሄሮች ማለትም በርታ ፣ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦ ፣ ኮሞ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ አገው፣ ካምባታ፣ ሃዲያ፣ ትግሬ፣ ጉራጌን ጨምሮ ሌሎችም እንደሚኖሩበት ቢታወቅም የክልሉ ህገ መንግስት ግን የአምስቱ ብቻ እንደሆነ ይተርካል። በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለአባይ የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃዱን ከታህሳስ 12/2015 ጀምሮ መስጠቱን በደብዳቤው ገልጧል። ይሁን እንጅ የፓርቲ ፍቃዱን የወሰዱትን እነ አቶ ይታያል በላይን ጨምሮ በርካታ አደራጆች እና አባላት በመሳደድ ላይ እንደሚገኙ አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ከምንጮች ለመረዳት ችሏል። አሚማ ያነጋገራቸው አቶ ይታያል በላይ በአዲስ አበባ ጉለሌ ክ/ከተማ ከሚኖሩበት አካባቢ ድረስ የተላከ ኃይል እያሳደዳቸው በመሆኑ ከቤታቸው ከወጡ ሶስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ አደራጆች እና አባላት እየታሰሩባቸው መሆኑን የጠቆሚት አቶ ይታያል እንደአብነት ሲጠቅሱም:_ 1) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ወንበራ ወረዳ ሰንኮፍ ቀበሌ የፓርቲው አባል አቶ ቢረሳው ገመቹ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም. መታሰራቸውን፣ በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ አንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር እንዲሁ በትእዛዝ ታስሮ የነበረ ሲሆን በ6ኛ ቀኑ የፌድራል ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባደረገው ጥረት ግለሰቡ ተፈቷልም ብሏል። 2) በእለቱም የድጋፍ ፊርማ ሲያስፈርሙ የነበሩትን አባላት የድጋፍ ፊርማ ሰነዶቻቸውን የወረዳው ፖሊስ እንደቀማቸው፤ 3) አቶ ፈቀደ ሹሞን እና አቶ አበበ ቶሎሳ በተባሉ አባላቱ ላይ የወረዳው አመራር እንደዛተባቸው ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ተመላክቷል። 4) መምህር ፍቅረ ስላሴ አካሉ፣ በአሶሳ ዩኒቨርስቲ የመምህራን ማህበር ሰብሳቢ፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር እና የአልማ የወጣቶች ጉዳይ ተጠሪም ከየካቲት 6/2015 ጀምሮ መታሰሩን ፓርቲው ለአሚማ አስታውቋል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ አሻድሌ ሀሰን፣ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ የሆኑት አቶ ይስሃቅ አብዱል ቃድር እና ሌሎችም ከምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ እውቅና ያገኘውን ፓርቲ በሀሰት ስሙን በማጥፋት “የመተከል አስመላሽ ኮሚቴ ነው፣ ከአማራ ክልል ተልዕኮ የተሰጠው ነው” በማለት አመራር እና አባላቱን እያሳደዱ ይገኛሉ የሚል ቅሬታ ቀርቦባቸዋል። አሚማ የክልሉ ፕሬዝደንት አቶ አሻድሌ ሀሰን እና የብልጽግና ኃላፊው አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር በተነሳው ቅሬታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በሚል በእጅ ስልካቸው ላይ የደወለ ቢሆንም የአቶ አሻድሌ ስልክ የማይሰራ ሲሆን፣ አቶ ይስሃቅ ደግሞ የሚጠራ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ለጊዜው ሀሳባቸውን ለማካተት አልቻለም።
Source: Link to the Post