በምስራቅ ሐረርጌ በጫት ላይ የተጣለው ከፍተኛ ቀረጥ ነጋዴውን እየተፈታተነ ነው

      በምስራቅ ሐረርጌ ዞን “ጫት አምራች” የተባሉ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ በመወሰኑ ሳቢያ፣ ጫት አምራች ገበሬዎችና ነጋዴዎች ለስደት መዳረጋቸው ተሰምቷል፡፡ በጫት ምርት ላይ የተጣለው ከፍተኛ ቀረጥ በጫት ንግድ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ ዜጎች የዕለት ጉርሳቸውን እንኳን ለማግኘት ተፈታትኗቸዋል ነው የተባለው፡፡

ከሁለት ዓመታት ወዲህ ተወስኗል የተባለው ከፍተኛ የጫት ቀረጥ ባስከተለው ጫና፣ ገበሬዎች ለነጋዴዎች ጫት የሚያስረክቡበትን ዋጋ እንዲያረክሱ እንዳስገደዳቸው የዞኑ ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። በአንድ ኪሎ ግራም ጫት ከፍ ያለ ቀረጥ መጣሉን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ይህም ከፍተኛ ቀረጥ ጫናውን አምራች ገበሬዎች ላይ ማሳረፉን አስረድተዋል።
“ቀረጡ የተወሰነው ከሁለት ዓመታት ወዲህ ነው” የሚሉት ነዋሪዎች፣ ይህም በሕጋዊ መንገድ  ወደ ሶማሊያ (ሞቃዲሾ)፣ ሶማሊላንድና ፑንትላንድ የሚላከውን የጫት መጠን በእጅጉ እንደቀነሰው ይገልጻሉ።
አቶ አብዲሳ የተባሉ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በጫት ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ እንደ ገለፁት፣ ቀደም ሲል ለጫት የሚከፈለው ቀረጥ በአንድ ኪሎግራም 5 ዶላር ነበር።
ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን ወደ ሶማሊያ የሚላከው ጫት ላይ በአንድ ኪሎግራም 10 ዶላር (570 ብር ገደማ) ቀረጥ መጣሉ፣ በነጋዴው ላይ ጫና በመፍጠሩ ጫትን ከገበሬዎች በርካሽ ዋጋ እንዲረከብ ማድረጉን  ይገልጻሉ። ቀረጡን ላለመክፈል ሲሉም በርካታ ነጋዴዎች ሕገ ወጥ አካሄድ መምረጣቸውንም ጠቁመዋል።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያደረገው ጥናት ለዚህ ከፍተኛ የቀረጥ ጭማሪ አስተዋጽዖ ማድረጉን የሚናገሩት ነጋዴው፤ በተለይ ጥናቱን ባደረገው ቡድን ውስጥ የተካተቱት ባለሙያዎች “ስለጫት አመራረትና የሽያጭ ሂደት ጥልቅ ዕውቀት የሌላቸው መሆናቸው”  ለችግሩ ያስረዳሉ፡፡
“ቀደም ሲል ጫት ወደ ሶማሊያ ተወስዶ፣ በዶላርም፤ በሶማሊያ ሽልንግም፤ በብርም ይሸጥ ነበር። ነጋዴው ሁሉ ከዚያ ሽያጭ የተገኘውን ብር ሰብስቦ፣  ወደ ባንክ ያስገባል። ይሁንና የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ነጋዴው ሕገ ወጥ ንግድን መረጠ” ብለዋል – አቶ አብዲሳ ለአዲስ አድማስ።
በሌላ በኩል፣ መንግስት ከምስራቅ ኦሮሚያ ዞኖች ወደ ሶማሊያ ክልል በቀን የሚገባው የጫት መጠን ወደ 17 ሺህ እንዲወርድ ወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ የጫት ኮታው ወደ 127 ሺህ ኪሎግራም እንዲመለስ መደረጉን አቶ አብዲሳ ያወሳሉ። ግን ውሳኔው የጫት ዋጋን ከመርከስ አላዳነውም ይላሉ።

ይህም ሕገ ወጥ ንግድ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ያቋቋማቸውን ኬላዎች ጥሶ በማለፍ የሚከወን እንደሆነ ነጋዴው ያብራራሉ። ንግዱን ለማቀላጠፍ ሲባል፣ ለአንድ ‘አይሱዙ’ የጭነት መኪና እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ በየኬላው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ጉቦ እየተሰጠ እንደሚታለፍ ነጋዴው ጠቅሰዋል።
የጫት ቀረጡ ምዕራብ እና ምስራቅ ሐረርጌ ላይ ተጽዕኖውን ቢያሳርፍም፣ በተለይ ምስራቅ ሐረርጌ ላይ ያደረሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን አቶ አብዲሳ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል። “የጫት ምርቱን ወደ ሶማሊያ በብዛት የሚልከውና፣ ሌሎች አማራጭ ምርቶችን የማያመርተው የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ስለሆነ፣ ጉዳቱ የከፋ ሆኖበታል።” ብለዋል።
በጋራ ሙለታ፣ ኦቦራ፣ ፈዲስ እና ጃርሶ አካባቢዎች የሚኖሩ ጫት አምራች ገበሬዎች የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እያዳገታቸው መምጣቱ የጠቀሱት የዞኑ ነዋሪዎች፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ ሐረር፣ ድሬደዋ፣ አዲስ አበባና ጅግጅጋ መሰደዳቸውንም ተናግረዋል።

እነዚሁ ጫት አምራች ገበሬዎች ከዚህ በፊት ለጫት ምርት ስራ የሚጠቀሙባቸውን የውሃ ፓምፕና ጄኔሬተሮች፣ እንዲሁም የመኖሪያ ቤታቸውን የብረት በር ከመሸጥ አንስቶ እስከ ማገዶ እንጨት ለቀማ ድረስ የጉልበት ስራዎችን በመስራት የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እየጣሩ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ አክለው ገልፀዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደርም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጡም የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ችግሩ አስቸኳይ መፍትሔ ካልተበጀለት፣ ችግሩ እየሰፋና እየከፋ እንደሚመጣ ነው ያስጠነቀቁት።
በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ምስራቅ ሐረርጌ አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ ዘንድ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም፣ ሙከራችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply