በምስራቅ አርሲ ዞን ለመንቀሳቀስ የሞከረው የአሸባሪው የሸኔ ቡድን አባላት ላይ ወታደራዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ተገለጸበኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን ካሉት አስራ አምስት ወረዳዎች…

በምስራቅ አርሲ ዞን ለመንቀሳቀስ የሞከረው የአሸባሪው የሸኔ ቡድን አባላት ላይ ወታደራዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን ካሉት አስራ አምስት ወረዳዎች በምስራቅ አርሲን በሚዋሰኑት እንደ የሄበን አርሲ ወረዳ ባሉ ወረዳዎች አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የአሸባሪው የሸኔ ቡድን አባላትን የሚያከስም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የምዕራብ አርሲ ዞን ፀጥታ ቢሮ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልጸዋል፡፡

‘‘እኛ ከዚህ ቡድን ጋር ያልተወራረደ ሂሳብ አለን” ያሉት ምክትል ኃላፊው አቶ ኡመር ‘‘ብዙ የዚህ አካባቢ ተወላጆች በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለግዳጅ ሲንቀሳቀሱ የአርሲ ጎሳ ናችሁ በሚል ተለይተው ሲገደሉ ነበር ” ብለዋል፡፡

ሸኔዎች በአባገዳዎች እና በአደ ሲንቄዎች መወገዙን የሚናገሩት አቶ ኡመር ‘‘የጉማ ሰው ተብለው ስለተፈረጁ እዚህ እኛ ጋር ምንም ተቀባይነት የላቸውም ” ብለዋል፡፡

‘‘ በሌሎች ዞኖች ያለው ምቹ ሁኔታ እዚህ የለም” ያሉት ምክትል ኃላፊው ፣በሌሎች አካባቢዎች የሚያገኙት የፋይናንስ ፣ የምግብ እና የመረጃ ምንጭ እኛ ጋር ደረቀ በመሆኑ ዞናችን ሰላም ነው” ይላሉ፡፡

አሁን እየተደረገ ያለው ዘመቻም ውጤት እያመጣ መሆኑን አንስተው በዞኑ ባሉ 36 ኬላዎችም ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን የሄበን አርሲ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ በሪሶ ቡልዬ እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡

የዞኑ ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡመር ቲናኦብሲ ለጣቢያችን እንዳሉት በምዕራብ አርሲ ዞን የሸኔ አባል ነኝ በሚል ወደ ካምፕ ገብቶ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሉም ብለዋል፡፡

ያይኔአበባ ሻምበል
ታህሳስ 19 ቀን 2014 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply