በምስራቅ ወለጋ ዞን እንዲሰፍር የተደረገው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል ተባለ

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን በአንገር ጉትን ከተማ እና አካባቢው ከጥቂት ቀናት ወዲህ መልሶ እንዲሰፍር የተደረገው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አሳሳቢ ሁኔታን ፈጥሯል ሲል እናት ፓርቲ በትናንትናው ዕለት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ፓርቲው አክሎም “ልዩ ኃይሎች ፈርሰዋል” በተባለበት ሁኔታ፤ በዩኒፎርም እና ሙሉ ትጥቅ ድንገት በአካባቢው መጥቶ መስፈሩ፣ መፍረሱን ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱ በተጨማሪ የአካባቢውን ነዋሪ እንዳይረጋጋ በማድረግ ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሏል ነው ያለው።

ይህ ጉዳይ “ለምን” የሚል ጥያቄ እንደሚያስነሳ በመጥቀስም፤ በአካባቢው መልሶ እንዲሰፍር የተደረገው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ለምን መስፈር እንዳስፈለገው ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥበትና ከቦታው ተነስቶ ለነዋሪው ስጋት የማይሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር አሳስቧል።

“አገር ከበቂ በላይ ችግር ስለተሸከመች የተጨማሪ ግጭት ጠመቃ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ይቁም” ያለው ፓርቲው፤ “መንግሥት ችግሮችን በውይይት ብቻ እንዲፈታ በተደጋጋሚ አጥብቀን እየጠየቅን ባለንበት በዚህ ሰዓት፣ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የግጭት ጠመቃ እንቅስቃሴዎች ተበራክተዋል።” ብሏል።

እንዲሁም በጋምቤላ ክልል በአኝዋክ እና ኑዌር ጎሳዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ደም አፋሳሽ ሆኖ በመቀጠሉ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወገኖች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ነው የገለጸው።

በዚሁ ክልል የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር አልፈው በሕዝባችን ላይ ጥቃት እየፈጸሙና የዜጎቻችንን ሕይወት እየቀጠፉ ቢሆንም፤ አገር ጥቃት እየደረሰባት እየተወሰደ ያለ ተግባራዊ የሆነ አጸፋዊ እርምጃ ስለመኖሩ ምንም ዓይነት ፍንጭ አለመታየቱና መንግሥት ዝምታን መምረጡ ከፍተኛ ጥያቄ ያጭራል ሲልም አስገንዝቧል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማም ከሱዳን ተነስቶ ከነትጥቁ ከተማ ገብቶ እንዲሰፍር የተደረገውና ባለፉት ቀናት ከሃያ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነው “ታጣቂ ኃይል” በሰላማዊ የማህበረሰቡ ነዋሪዎች ላይ ትልቅ ስጋትን ደቅኗል ነው የተባለው።

በመቶዎች የሚቆጠረው የታጣቂ ኃይሉ አባላትም ከትናንት ሌሊት ጀምሮ ከሰፈሩበት ካምፕ ከነትጥቃቸው ወጥተው ጠፉ መባሉ፤ በአካባቢው እየሆነ ካለው ነገር ጀርባ ሊኖር የሚችለውን ሴራ በግልጽ ያመላክታል ሲል ፓርቲው አክሏል።

ስለሆነም መንግሥት ከነሙሉ ትጥቁ በካምፕ እንዲቀመጥ ያደረገውና አሁን ላይ መጥፋቱ የተነገረው ታጣቂ ኃይል በአሁኑ ሰዓት በነዋሪዎች ላይ ትልቅ የአደጋ ስጋት የደቀነ መሆኑ ታውቆ፤ መከላከያ ሠራዊት አስፈላጊውን የዜጎች ደኅንነት የመጠበቅ ሥራ በመሥራት የሰፈነውን ሥጋት እንዲያስወግድ እናት ፓርቲ በመግለጫው ጠይቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply