በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አስተዳደር ከተመረቁት ፋኖዎች መካከል ሁለቱ ታሰሩ፤ ይፈቱልን ብለው ለመጠየቅ ወደ ብአዴን ጽ/ቤት ያቀኑ ከ70 ያላነሱ ወጣቶች ፍትህ እንዳልተሰጣቸውም እየገለፁ…

በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አስተዳደር ከተመረቁት ፋኖዎች መካከል ሁለቱ ታሰሩ፤ ይፈቱልን ብለው ለመጠየቅ ወደ ብአዴን ጽ/ቤት ያቀኑ ከ70 ያላነሱ ወጣቶች ፍትህ እንዳልተሰጣቸውም እየገለፁ ነው። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ከቀደመው የእነ በረከት ብአዴናዊ እና ትሕነጋዊ እሳቤ መፋታት ያቃቸው በርካታ አይለወጤ አመራሮች ካሉበት ብዙ የአማራ አካባቢዎች አንዱ ምስራቅ ጎጃም ነው ይላሉ የሞጣ ከተማ ነዋሪዎች። ነዋሪዎች ሲቀጥሉ በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አስተዳደር ቅሬታ ከተነሳባቸው አንዱ ኮማንደር ጌትነት ይባላሉ። ህዝብ በከፈለው መስዋዕትነት አልሳካላቸው ብሎ እንጅ ፀረ አማራ የሆነውን ህወሐት ጨፌ ጎዝጉዘው ሊቀበሉ ከነበሩት አንዱ የሞጣ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ ኮማንደር ጌትነትና መሰሎቻቸው እንደሆኑ ተገልጧል። ሌላኛው የሞጣ ከተማ ነዋሪ መስከረም 6 ቀን 2014 እነ ታጋይ ዘመነ ካሴ እና ጠበቃ አስረስ ማረ ዳምጤ በተገኙበት ከ100 በላይ ሰልጣኝ ፋኖዎች በሞጣ ከተማ ሰባቱ ዋርካ ላይ መመረቃቸውን አውስቷል። የመስተዳድር አካላት ጭምር በምርቃቱ እንዲገኙ ጥሪ እንደተደረገላቸው የገለፀው ምንጫችን ከተመረቁት ፋኖዎች መካከልም ሁለት እንደታሰሩ፤ ይፈቱልን ብለው ለመጠየቅ ወደ ብአዴን ጽ/ቤት ያቀኑ ከ70 ያላነሱ ወጣቶች አሁንም ሰሚ ማጣታቸውን አክለው ተናግሯል። የመንግስትን የዘመቻ ሕልውናን ጥሪ መሰረት በማድረግ ለ2 ወራት በአካባቢው ተቆርቋሪ ወጣቶችና በፋኖዎች ትብብር ሰልጥነው ከተመረቁት መካከል ትናንት አመሻሹን የታሰሩት 2 ወጣቶች ገደፋዬ አገኘ እና ዘላለም ይባላሉ። በርካታ የከተማው ነዋሪዎችና ወጣቶች በምርቃት ዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል። ለፋኖዎች ጥሩ እይታ የላቸውም፣ የትሕነግ መረብ አላቸው፣ ወጣቶችን እያሰቃዩ፣ እያሰሩ፣ እያሳደዱ ነው፣ የሚል ቅሬታ ከሞጣ ከተነሳባቸው አመራሮች መካከል አሳሪ ናቸው የተባሉትን ኮማንደር ጌትነትን ለማግኘት አሚማ ደጋግሞ በእጅ ስልካቸው ላይ ደውሏል። ይሁን እንጅ አንዴ ብቻ አንስተው የአሚማ ጋዜጠኛ መሆንህን ስለማላውቅ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለሁም በሚል ስልካቸውን ዘግተዋል፤ ደጋግመን ከመደወል ባሻገር መልዕክት የጻፍንላቸው ቢሆንም መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲሰሩ የነበሩ 3 ወጣቶች ነሃሴ 27 ቀን 2013 መታሰራቸውን ተከትሎ አሚማ የወረዳ ፖሊስ አዛዥ ናቸው የተባሉት ዋና ኢንስፔክተር ደሳለኝን ማነጋገሩ አይዘነጋም። ለቀረበባቸው ቅሬታ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁት ኢንስፔክተር ደሳለኝም “በቢሮ ስልክ ካልደወልክ መረጃ አልሰጥም፤ እንድሰጥም ግዴታ የለብኝም” ከማለታቸው ባሻገር ከአንድ የፖሊስ አዛዥ ስነ ምግባር በማይጠበቅ መልኩ “በቃ አትጨቅጭቀኝ” ማለታቸው ይታወሳል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply