በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በሱዳንና በአሸባሪው ትሕነግ ቅንጅት በተፈጸመባቸው ወረራ የተፈናቀሉ አማራዎች የድጋፍ ጥሪ አቀረቡ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም…

በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በሱዳንና በአሸባሪው ትሕነግ ቅንጅት በተፈጸመባቸው ወረራ የተፈናቀሉ አማራዎች የድጋፍ ጥሪ አቀረቡ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ሱዳን ከአሸባሪው እና ከሃዲው ትሕነግ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ፣ መተማ እና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች ወርረው ከያዙ ቢያንስ 1 ዓመት ከ5 ወራት አልፏል። በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ከምድረ ገነት (አብደራፊ) በቅርብ ርቀት አቦጢር አካባቢ ሰላም በር የተባለች ከተማ በ2006 ዓ/ም በአብዛኛው በስራ አጥ ወጣቶች እና በመከላከያ ምልሶች ነበር የተቆረቆረችው። ይሁን እንጅ በታህሳስ 2013 አሸባሪውን ትሕነግ እንደ ምሽግ በመጠቀም የሱዳን መከላከያ ሰራዊት የቡድን መሳሪያ ጭምር በመጠቀም ሉአላዊነትን በመዳፈር የሰላም በር ከተማን ተቆጣጥሮ አውድሟታል፤ የቤተ ክርስቲያን ቆርቆሮ ሳይቀር አፍርሶ፣ ዘርፎ ወስዷል። በአካባቢው እያለሙ ይኖሩ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አማራዎች ለአንድ ወር ያህል ሰሚ ጠፍቶ በጎዳናው ሲንገላቱ ከቆዩ በኋላ ምድረገነት ላይ በአንድ መጠለያ ካምፕ እንዲገቡ ተደርጓል። ይሁን እንጅ እነዚህ ቁጥራቸው ከ350 በላይ የሚሆኑ አባዎራ እና እማዎራዎች በየወሩ ሲላክላቸው የነበረው የ15 ኪሎ ስንዴ ደረጋፍ ከተቋረጠባቸው ሁለት ወር እንደሆናቸው በኮሚቴዎቻቸው በኩል ተናግረዋል። የትንሳኤ በዓል እንኳ አንድም የወረዳ አመራር መጥቶ አልጎበኘንም፤ የደገፈን አካል የለም ሲሉ አማረዋል። የችግሩ ስፋት አሳሳቢ በመሆኑ ፍትህ እንፈልጋለን የሚመለከተው አካል ሊደግፈን ይገባል ብለዋል። ጊዜያዊ መታወቂያ እንኳ ቢሰጠን በሚል ብንማጸንም የሚረዳን አላገኘንም ብለዋል። የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ አያና በበኩላቸው ከድጋፍ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ችግር አዲስ መሆናቸውን ጠቅሰው የእርዳታውም ሆነ የመታወቂያው ጉዳይ መፍትሄ እንዲሰጥ እናደርጋለን ብለዋል። በተመሳሳይ ላለፉት ሁለት ወራት በተከታታይ ከራያ አላማጣ እና አካባቢው በአማራዊ ማንነታቸው የተፈናቀሉ ቁጥራቸው ከ60 ሽህ በላይ እንደሚሆኑ የገለጹ ተፈናቃዮች በራያ ቆቦ ተጠልለው በሚገኙበት ጃራ በቂ የሆነ የሰብአዊ ድጋፍ እየደረሳቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል። ከአሸባሪው ትሕነግ የተደራጀ የወረራ ጥቃት ሸሽተው ነው ወደ ራያ ቆቦ ለመድረስ የቻሉት። እነዚህ ተፈናቃዮች የምግብ ዋስትና እና አደጋ መከላከል ተገቢ የሆነ ሰዋዊ እርዳታ እያደረሰልን ባለመሆኑ ክፉኛ ተቸግረናል ብለዋል። አካባቢው መብራት፣ውሃ፣በቂ ህክምና የሌለው በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚመጣው የስንዴ እርዳታም መጠኑ በቂ አይደለም ብለዋል። የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ ተማጽነዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply