በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አስተዳደር ደለሎ ቀበሌ ከ8 ወራት በፊት የግድያ ወንጀል በፈፀመ ግለሰብ ላይ 19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ተላለፈበት፡፡ አማራ ሚዲያ ማዕከል/…

በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አስተዳደር ደለሎ ቀበሌ ከ8 ወራት በፊት የግድያ ወንጀል በፈፀመ ግለሰብ ላይ 19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ተላለፈበት፡፡ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ አቶ ክንዱ ምህረቱ ይባላል፤ ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት ተነስቶ በ1997 ዓ.ም ነበር ወደ መተማ ወረዳ ለስራ ጉዳይ የመጣው። ለወደፊት ያለውን ራዕይ ለማሳካት በሚልም በመተማ ወረዳ ደለሎ የእንሰሳትና የእርሻ ኢንቨስትመንት አካባቢ ልዩ ቦታው ጠቅላይ ጎራ ተብሎ በሚጠራው ከ170 በላይ በግ እያረባ ነበር። የእንሰሳት እርባታውንም ያግዘኛል፣ ይረዳኛል እሱም ተጠቃሚ ይሆናል ከሚል በጎ አስተሳሰብ አቶ እያያው መብራቱ የተባለን የአጎቱን ልጅ በማስመጣት በጋራ ሰርተው ለማደግ እንቀስቃሴ ጀመሩ፡፡ ሆኖም ግን ጥር ወር 2012 ዓ.ም አቶ ክንዱ ምህረቱ ባልጠበቀው እና ባልገመተው ሁኔታ የአጎቱ ልጅ በሆነው በአቶ እያያው መብራቱ ግድያ ተፈፅሞበት ላለፉት 8 ወራትም በህይወት አለመኖሩ ሳይታወቅ ቆይቷል፡፡ ወንጀሉ ስለመፈፀሙ ጥቆማ የደረሰው የመተማ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ባደረገው ጠንካራ ክትትል ተይዟል፤ የምርመራ ሂደቱም መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም አቶ እያያው መብራቱ አቶ ክንዱ ምህረቱን መግደሉን አምኖ ቃሉን በመስጠቱ መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም ገድሎ የቀበረበትን ቦታ አሳዬ፤ የሟች አፅምም እንዲወጣ ተደርጎ ደለሎ ቁጥር አንድ መዳኅኒያዓለም ቤተ ክርስቲያን በክብር ስርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል፡፡ የወረዳው የፖሊስ ኃይል አባላት ወንጀለኛው በህግ ከመያዙ በፊት የተደረገው ጠንካራ ክትትል እና ምርመራ እንዲሁም ከተያዘ በኋላ ተገቢውን የህግ ቅጣት እዲያገኝ የምርመራውን እና ክትትል ሂደቱን አስረድተዋል። ዋና ሳጅን ዘመነ ነጋሸ የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ የኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች ንዑስ ክፍል ኃላፊ ሟች አቶ ክንዱ ምህረቱ በአካባቢው ባለመኖሩ ምክንያት ነሃሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በቤተሰቦች አማካኝነት ለፖሊስ ጽህፈት ቤቱ ጥቆማው መድረሱን እና በደለሎ የእርሻ ኢንቨስትመንት አካባቢ ልዩ ቦታው ጠቅላይ ጎራ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ሟች አቶ ክንዱ ምህረቱ እና የግድያ ወንጀል የፈፀመው አቶ እያያው መብራቱ በጋራ በግ እያረቡ እደነበር መረጃውን በማጥናት የተጠናከረ ክትትል እና ምርመራ በማድረግ ወንጀለኛውን በህግ ቁጥጥር ስር አውለው የህግ ውሳኔ እንዲያገኝ ማስቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ የወንጀል ምዝገባ እና ክትትል ሳጅን ዮርዳኖስ ደጉ የተፈፀመውን የግድያ ወንጀል ፖሊሳዊ አካሄዶችን በመጠቀም በቡድን የተጠናከረ ምርመራ ተደርጎ በአጭር ጊዜ ለህግ ቀርቦ በ19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ኢንስፔክተር ጌታቸው ባየ የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የቴክኒክ ምርመራ ክፍል ሀላፊ የተፈፀመው ወንጀል ውስብስብ እና በእጅጉ አስቸጋሪ ነበር ይላሉ፡፡ ሟች አቶ ክንዱ ምህረቱ እና የግድያ ወንጀል የፈፀመው አቶ እያያው መብራቱ ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ የመጡ እና ዝምድና ያላቸው ቤተሰብ ሲሆኑ ሟች አቶ ክንዱ መብራቱ ለስራ ታታሪ እና ስራ ወዳድ ለልማት እና ዕድገት በነበረው ፍላጎት አንፃር ሁሌም የሚተጋ እንደነበር በቅርብ አብረውት ከኖሩ ሰዎች መረዳት ተችሏል ብለዋል፡፡ የአጎቱ ልጅ የሆነውን አቶ እያያው መብራቱን ወደ እሱ አምጥቶት ሟች ጀምሮት የነበረውን በግ የማርባት ስራ በጋራ እየሰሩ እያለ በሰይጣናዊ ቅናት ብገለው ያሉትን በጎች እና ንብረቱን የግሌ ማድረግ እችላለሁ በሚል ሃሳብ እንደገደለው በምርመራ ሂደቱ ከአንደበቱ መረዳታቸውን ነው ኢንስፔክተር ጌታቸው የገለፁት፡፡ በመሆኑም የሰራተኛ ቅጥር በምንፈፅምበት ጊዜ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ እና አንድ ሰው ከመኖሪያ ቦታው ለረዥም ጊዜ ከተሰወረ ለፖሊስ እና ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አንስፔክተር ወለላው ተገኘ የመተማ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በወረዳው የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በተቀናጀ እና በብቃት በመምራት የተጠናከረ ክትትል እና ምርመራ በመደረጉ ወደ ህግ እየቀረቡ ውሳኔ እያገኙ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ለዚህም ከ8 ወራት በፊት የግድያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ የቅጣት ውሳኔ እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ የመተማ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን

Source: Link to the Post

Leave a Reply